1 ነገሥት 19:3-12

1 ነገሥት 19:3-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኤል​ያ​ስም ፈርቶ ተነሣ፤ ነፍ​ሱ​ንም ሊያ​ድን ሄደ፤ በይ​ሁ​ዳም ወዳ​ለው ወደ ቤር​ሳ​ቤህ መጥቶ ብላ​ቴ​ና​ውን በዚያ ተወ። እር​ሱም አንድ ቀን የሚ​ያ​ህል መን​ገድ በም​ድረ በዳ ሄደ፤ መጥ​ቶም ከደ​ድሆ ዛፍ በታች ተቀ​መ​ጠና፦ ይበ​ቃ​ኛል፤ አሁ​ንም አቤቱ! እኔ ከአ​ባ​ቶቼ አል​በ​ል​ጥ​ምና ነፍ​ሴን ውሰድ” ብሎ እን​ዲ​ሞት ለመነ። በደ​ድ​ሆ​ውም ዛፍ በታች ተኛ፤ እን​ቅ​ል​ፍም አን​ቀ​ላፋ፤ እነ​ሆም፥ መል​አክ ዳሰ​ሰ​ውና፥ “ተነ​ሥ​ተህ ብላ” አለው። ከዚህ በኋላ ኤል​ያስ ተነ​ሥቶ፥ እነሆ፥ በራሱ አጠ​ገብ የተ​ጋ​ገረ እን​ጎ​ቻና በማ​ሰሮ ውኃ አገኘ። በላም፤ ጠጣም፤ ተመ​ል​ሶም ተኛ። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አክ ደግሞ ሁለ​ተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰ​ሰ​ውና፥ “የም​ት​ሄ​ድ​በት መን​ገድ ሩቅ ነውና ተነ​ሥ​ተህ ብላ” አለው። ተነ​ሥ​ቶም በላ፤ ጠጣም፤ በዚ​ያም በበ​ላው የም​ግብ ኀይል እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። እዚ​ያም ወዳለ ዋሻ ገባ፤ በዚ​ያም አደረ፤ እነ​ሆም፥ “ኤል​ያስ ሆይ! ምን አመ​ጣህ?” የሚል የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። ኤል​ያ​ስም፥ “ሁሉን ለሚ​ገዛ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እጅግ ቀን​ቻ​ለሁ፤ የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ቃል ኪዳ​ን​ህን ትተ​ዋ​ልና፥ መሠ​ዊ​ያ​ዎ​ች​ህ​ንም አፍ​ር​ሰ​ዋ​ልና፥ ነቢ​ያ​ት​ህ​ንም በሰ​ይፍ ገድ​ለ​ዋ​ልና፤ እኔም ብቻ​ዬን ቀር​ቻ​ለሁ ነፍ​ሴ​ንም ሊወ​ስ​ዱ​አት ይሻሉ” አለ። እር​ሱም አለ፥ “ነገ ውጣ፤ በተ​ራ​ራ​ውም ላይ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ቁም። እነ​ሆም፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዚያ አለፈ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ትል​ቅና ብርቱ ነፋስ ተራ​ሮ​ቹን ሰነ​ጠቀ፤ ዓለ​ቶ​ቹ​ንም ሰባ​በረ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን በነ​ፋሱ ውስጥ አል​ነ​በ​ረም። ከነ​ፋ​ሱም በኋላ የም​ድር መና​ወጥ ሆነ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን በም​ድር መና​ወጥ ውስጥ አል​ነ​በ​ረም። ከም​ድር መና​ወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ሳቱ ውስጥ አል​ነ​በ​ረም። ከእ​ሳ​ቱም በኋላ እንደ ፉጨት ያለ ቀጭን ድምፅ ሆነ፤ በዚ​ያም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነበረ።

1 ነገሥት 19:3-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኤልያስም ፈርቶ ስለ ነበር፣ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ። በይሁዳ ምድር ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ እንደ መጣም አገልጋዩን በዚያ ተወው፤ በምድረ በዳም ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ወደ አንድ ክትክታ ዛፍ እንደ መጣም፣ ከሥሩ ተቀምጦ፣ ይሞት ዘንድ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” ብሎ ጸለየ። ከዚያም ከዛፍ ሥር ተጋደመ፤ እንቅልፍም ወሰደው። በድንገትም አንድ መልአክ ነካ አደረገውና፣ “ተነሥና ብላ” አለው። ዘወር ብሎ ሲመለከትም፣ እነሆ፣ በፍም የተጋገረ ዕንጐቻና አንድ ገንቦ ውሃ ከራስጌው አገኘ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ። የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና መጥቶ ነካ አደረገውና፣ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ ተነሥና ብላ” አለው። ስለዚህም ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ፤ በዚያም ወደ አንዲት ዋሻ ገብቶ ዐደረ። እግዚአብሔር የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እርሱ መጣ፤ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው። እርሱም፣ “እኔ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ” አለ። እግዚአብሔርም፣ “እግዚአብሔር በዚያ ያልፋልና ወደ ተራራው ወጥተህ በእግዚአብሔር ፊት ቁም” አለው። ከዚያም ታላቅና ኀይለኛ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤ ዐለቶችንም በእግዚአብሔር ፊት ብትንትናቸውን አወጣ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ከነፋሱም ቀጥሎ የምድር መነዋወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መነዋወጡ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መነዋወጡም ቀጥሎ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም ቀጥሎ ለስለስ ያለ ድምፅ ተሰማ።

1 ነገሥት 19:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፤ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፤ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ። እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና “ይበቃኛል፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ፤” ብሎ እንዲሞት ለመነ። በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋደመ፤ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና “ተነሥተህ ብላ፤” አለው። ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውሃ አገኘ። በላም፤ ጠጣም፤ ተመልሶም ተኛ። የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ፤” አለው። ተነሥቶም በላ፤ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኀይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ። እነሆም “ኤልያስ ሆይ! በዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። እርሱም “ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ፤” አለ። እርሱም “ውጣ፤ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም፤” አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዐለቶቹንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ።

1 ነገሥት 19:3-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኤልያስም ስለ ፈራ ሕይወቱን ለማትረፍ ከአገልጋዩ ጋር በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ ከተማ ሄደ። አገልጋዩንም በዚያ ተወው፤ ኤልያስ አንድ ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዘ፤ ከዚህ በኋላ ጒዞውን ቆም አድርጎ፥ በአንድ የክትክታ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጠ፤ ሞቱንም በመመኘት “እግዚአብሔር ሆይ! አሁንስ ይብቃኝ፤ ከቀድሞ አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ!” ሲል ጸለየ። ከዚህ በኋላ በዛፉ ሥር ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው፤ በድንገትም አንድ መልአክ መጥቶ በመዳሰስ ቀሰቀሰውና “ተነሥ ብላ!” አለው፤ ኤልያስም ተነሥቶ ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ በድንጋይ ሙቀት የበሰለ የዳቦ ሙልሙልና አንድ ገንቦ ውሃ በራስጌው ተቀምጦ አየ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ተመልሶ መጥቶ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ፥ ተነሥተህ ብላ!” ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው፤ ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኀይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ፤ እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ። በድንገትም እግዚአብሔር “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ!” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ እግዚአብሔር ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም፤ ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ።

1 ነገሥት 19:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኤልያስም ስለ ፈራ ሕይወቱን ለማትረፍ ከአገልጋዩ ጋር በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ ከተማ ሄደ። አገልጋዩንም በዚያ ተወው። ኤልያስ አንድ ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዘ፤ ከዚህ በኋላ ጉዞውን ቆም አድርጎ፥ በአንድ የክትክታ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጠ፤ ሞቱንም በመመኘት “ጌታ ሆይ! አሁንስ ይብቃኝ፤ ከቀድሞ አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ!” ሲል ጸለየ። ከዚህ በኋላ በዛፉ ሥር ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው፤ በድንገትም አንድ መልአክ መጥቶ በመዳሰስ ቀሰቀሰውና “ተነሥ ብላ!” አለው፤ ኤልያስም ተነሥቶ ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ በድንጋይ ሙቀት የበሰለ የዳቦ ሙልሙልና አንድ ገንቦ ውሃ በራስጌው ተቀምጦ አየ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ። የጌታም መልአክ ተመልሶ መጥቶ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ፥ ተነሥተህ ብላ!” ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው። ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኃይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ። እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ። በድንገትም ጌታ “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ!” ሲል መለሰ። ጌታም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ጌታ በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረብቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ ጌታ ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ ጌታ ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ ጌታ ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ።