1 ቆሮንቶስ 7:36-40
1 ቆሮንቶስ 7:36-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ሰው ያጫትን ድንግል በአግባቡ ካልያዘ፣ እርሷም በዕድሜ እየገፋች ከሄደች፣ ሊያገባት ካሰበ የወደደውን ያድርግ፤ ኀጢአት የለበትምና ይጋቡ። ነገር ግን በዚህ ጕዳይ ልቡን አረጋግቶ፣ ሳይናወጥ፣ ራሱንም በመግዛት ድንግሊቱን ላለማግባት የወሰነ ሰው መልካም አድርጓል። ስለዚህ ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባም የተሻለ አደረገ። አንዲት ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ ከርሱ ጋራ የታሰረች ናት፤ ባሏ ቢሞት ግን፣ የፈለገችውን ሰው ለማግባት ነጻነት አላት፤ ሰውየው ግን በጌታ መሆን አለበት። እንደ እኔ ከሆነ ግን ሳታገባ እንዲሁ ብትኖር ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለች፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል።
1 ቆሮንቶስ 7:36-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ። ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ። እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ። ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት። እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።
1 ቆሮንቶስ 7:36-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ሰው እጮኛውን ላለማግባት ከወሰነ በኋላ ይህን ማድረጉ ለልጅትዋ መልካም ያላደረገ መሆኑ ቢሰማው፥ ከዚህም ሌላ እርስዋን ለማግባት ያለው ፍላጎት ጠንካራ ቢሆንና መጋባታቸውም ትክክል ከመሰለው እንደ ተመኘው ቢያገባት ኃጢአት አይሆንበትም፤ ስለዚህም ይጋቡ። ነገር ግን አንድ ሰው በልቡ ከጸና፥ አስገዳጅ ነገር ከሌለበት፥ ፍላጎቱን ለመቈጣጠር ከቻለና እጮኛውን ላለማግባት ከወሰነ መልካም አደረገ። ስለዚህ ሚስት የሚያገባ መልካም ያደርጋል፤ የማያገባ ግን የተሻለ ያደርጋል። ሚስት ባልዋ በሕይወት እስካለ ድረስ በጋብቻ ሕግ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ከሞተ ግን የፈለገችውን ለማግባት ነጻ ነች፤ ሆኖም የምታገባው ሰው ክርስቲያን መሆን አለበት። በእኔ አስተያየት ግን ባል ሳታገባ ብቻዋን ብትሆን ይበልጥ ተደስታ ትኖራለች፤ እኔም የእግዚአብሔር መንፈስ ያለኝ ይመስለኛል።
1 ቆሮንቶስ 7:36-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሸመገለ ጊዜ ስለ ድንግልናው እንደሚያፍር የሚያስብ ሰው ቢኖር እንዲህ ሊሆን ይገባል፤ የወደደውን ያድርግ፤ ቢያገባም ኀጢአት የለበትም። በልቡ የቈረጠና ያላወላወለ ግን የወደደውን ሊያደርግ ይችላል፤ ግድም አይበሉት፤ ድንግልናውንም ይጠብቅ ዘንድ በልቡ ቢጸና መልካም አደረገ። ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባ ግን የምትሻለውን አደረገ። ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሠረች ናት፤ ባልዋ የሞተ እንደ ሆነ ግን ነጻ ናት፤ የወደደችውን ታግባ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ይሁን። በምክሬ ጸንታ እንዲሁ ብትኖር ግን ብፅዕት ናት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል።
1 ቆሮንቶስ 7:36-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳሩ ግን አንድ ሰው በእጮኛው ላይ መልካም አለማድረጉን ቢያስብ፥ እጮኛውም ዕድሜዋ ለጋብቻ ከደረሰ፥ ሊያገባም ከፈቀደ፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ። ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ምንም አስገዳጅ የለበትም፤ ፍላጎቱን ለመቆጣጠር ከቻለና እጮኛውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ። ስለዚህ ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ፥ ያላገባም የተሻለ አደረገ። ሚስት ባሏ በሕይወት እስካለ የታሰረች ናት፤ ባሏ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት። እንደ እኔ አስተያየት ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።