ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 7
7
ስለ ጋብቻ
1ስለ ጻፋችሁልኝስ ለሰው ወደ ሴት አለመቅረብ ይሻለዋል። 2ነገር ግን እንዳትሴስኑ ሰው ሁሉ በሚስቱ ይወሰን፤ ሴትም ሁላ በባልዋ ትወሰን። 3ለሚስትም ባልዋ የሚገባትን ያድርግላት፤ እንዲሁ ሚስትም ለባልዋ የሚገባውን ታድርግለት። 4ሚስት በራስዋ አካል ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ባል በራሱ አካል ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። 5ለጸሎት እንድትተጉ ከምትስማሙበት ጊዜ ብቻ በቀር፥ ባልና ሚስት አትለያዩ፤ ዳግመኛ ሰይጣን ድል እንዳያደርጋችሁ በአንድነት ኑሩ፤ ሰውነታችሁ ደካማ ነውና ። 6ይህንም የምላችሁ እንደ ፈቃድ ነው እንጂ፥ ላዝዛችሁ አይደለም። 7ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ እግዚአብሔር እንደ አደለው ጸጋ ይኑር፤ ግብሩ እንዲህ የሆነ አለና፤ ግብሩ ሌላ የሆነም አለና።
8ነገር ግን ያላገቡትንና አግብተው የፈቱትን እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ ይሻላቸዋል እላለሁ። 9መታገሥ ባይችሉ ግን ያግቡ፤ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና። 10ያገቡትንም በእግዚአብሔር ትእዛዝ አዝዛቸዋለሁ፤ በራሴ ትእዛዝም አይደለም፤ ሚስትም ከባልዋ አትፋታ። 11#ማቴ. 5፥32፤ 19፥9፤ ማር. 10፥11-12፤ ሉቃ. 16፥18። ከተፋታችም ብቻዋን ትኑር፤ ያለዚያ ከባልዋ ጋር ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን አይፍታ።
12ሌላውን ግን ከራሴ እናገራለሁ፤ ከጌታችንም አይደለም፤ ከወንድሞቻችን መካከል የማታምን፥ ባልዋንም የምታፈቅር#“ባልዋን የምታፈቅር” የሚለው በግሪኩ የለም። ከእርሱም ጋር ለመኖር የምትወድ ሚስት ያለችው ሰው ቢኖር ሚስቱን አይፍታ። 13ሴቲቱም የማያምንና ሚስቱንም የሚያፈቅር#“ሚስቱን የሚያፈቅር” የሚለው በግሪኩ የለም። ከእርስዋም ጋር ሊኖር የሚወድ ባል ቢኖራት ባልዋን አትፍታ። 14የማያምን ባል በሚስቱ ይቀደሳልና፤ የማታምን ሚስትም በባልዋ ትቀደሳለችና፤ ያለዚያማ ልጆቻቸው ርኩሳን ይሆናሉ፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው። 15የማያምን ግን ቢፈታ ይፍታ፤ ወንድምና እኅት እግዚአብሔር ለሰላም ስለ ጠራቸው እንደዚህ ላለ ግብር አይገዙምና። 16ሚስትም ባልዋን ታድነው እንደ ሆነ አታውቅምና፤ ባልም ሚስቱን ያድናት እንደ ሆነ አያውቅምና።
17ነገር ግን ሁሉ እግዚአብሔር እንደ አደለው፥ ሁሉም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ እንዲህ ሥርዐት እንሠራለን። 18ተገዝሮ ሳለ የተጠራ ቢኖር አለመገዘርን አይመኝ፤ ያልተገዘረም ቢጠራ ከዚያ ወዲያ አይገዘር። 19የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ መገዘርም አይጠቅምም፤ አለመገዘርም አይጎዳም።
ወደ ሃይማኖት ስለ መጠራት
20ሁሉ እንደ ተጠራ እንዲሁ ይኑር። 21አንተ ባርያ ሳለህ ብታምን አያሳዝንህ፤ የሚቻልህ ከሆነ ግን ነጻነትህን አግኝ። 22የተጠራ ባሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነጻነት ያለው ነውና፤ እንዲሁ ነጻነት ያለውም ከተጠራ የክርስቶስ ባርያ ነው። 23በዋጋ ገዝቶአችኋልና የሰው ተገዦች አትሁኑ። 24ወንድሞቻችን ሁላችሁም በተጠራችሁበት እንዲሁ በእግዚአብሔር ኑሩ።
ስለ ደናግልና ስለ መዓስባት
25ስለ ደናግልም የምነግራችሁ የእግዚአብሔር ትእዛዝ አይደለም፤ ታማኝ እንድሆን እግዚአብሔር ይቅር ያለኝ እንደ መሆኔ ምክሬን እነግራችኋለሁ እንጂ። 26ነገር ግን እንዲህ ይመስለኛል፤ በግድ ይህ ሊመረጥ ይሻላልና እንዲህ ሆኖ ቢኖር ለሰው ይሻለዋል። 27ከሚስትህ ጋር ሳለህ ከእርስዋ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት ከሌለህ ግን ሚስትን አትሻ። 28ብታገባም ኀጢአት አይሆንብህም፤ ድንግሊቱም ባል ብታገባ ኀጢአት አይሆንባትም፤ ያገቡ ግን ለራሳቸው ድካምን ይሻሉ፤ እኔም ይህን የምላችሁ ስለማዝንላችሁ ነው። 29ነገር ግን ወንድሞቻችን እንዲህ ይቀናል፤ የዚህ ዓለም ኑሮ ሁሉ ሊያልፍ ቀርቦአልና፤ አሁንም ያገቡ እንዳላገቡ ይሆናሉ። 30ያለቀሱ እንዳላለቀሱ ይሆናሉ፤ ደስ ያላቸውም ደስ እንዳላላቸው ይሆናሉ፤ የሸጡም እንዳልሸጡ ይሆናሉ፤ የገዙም እንዳልገዙ ይሆናሉ። 31የበሉ እንዳልበሉ ይሆናሉ፤ የጠጡም እንዳልጠጡ ይሆናሉ፤ የዚህ ዓለም ተድላ ሁሉ ያልፋልና።
32እኔስ ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ፤ ያላገባ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኘው የእግዚአብሔርን ነገር ያስባልና። 33ያገባ ግን ሚስቱን ደስ ሊያሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ያስባል። 34እንዲህ ከሆነ ግን ተለያየ፤ አግብታ የፈታች ሴትም ያላገባች ድንግልም ብትሆን ነፍስዋም ሥጋዋም ይቀደስ ዘንድ እግዚአብሔርን ታስበዋለች፤ ያገባች ግን ባልዋን ደስ ልታሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ታስባለች። 35ይህንም የምላችሁ እንዲጠቅማችሁ ነው፤ ላጠምዳችሁ ግን አይደለም፤ ኑሮአችሁ አንድ ወገን እንዲሆንና እግዚአብሔርን ያለመጠራጠር እንድታገለግሉት ነው እንጂ።
36በሸመገለ ጊዜ ስለ ድንግልናው እንደሚያፍር የሚያስብ ሰው ቢኖር እንዲህ ሊሆን ይገባል፤ የወደደውን ያድርግ፤ ቢያገባም ኀጢአት የለበትም። 37በልቡ የቈረጠና ያላወላወለ ግን የወደደውን ሊያደርግ ይችላል፤ ግድም አይበሉት፤ ድንግልናውንም ይጠብቅ ዘንድ በልቡ ቢጸና መልካም አደረገ። 38ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባ ግን የምትሻለውን አደረገ።
39ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሠረች ናት፤ ባልዋ የሞተ እንደ ሆነ ግን ነጻ ናት፤ የወደደችውን ታግባ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ይሁን። 40በምክሬ ጸንታ እንዲሁ ብትኖር ግን ብፅዕት ናት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል።
Currently Selected:
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 7: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ