1 ቆሮንቶስ 7:25-35
1 ቆሮንቶስ 7:25-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ። እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ። ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር። ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል። ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።
1 ቆሮንቶስ 7:25-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለ ደናግልም የምነግራችሁ የእግዚአብሔር ትእዛዝ አይደለም፤ ታማኝ እንድሆን እግዚአብሔር ይቅር ያለኝ እንደ መሆኔ ምክሬን እነግራችኋለሁ እንጂ። ነገር ግን እንዲህ ይመስለኛል፤ በግድ ይህ ሊመረጥ ይሻላልና እንዲህ ሆኖ ቢኖር ለሰው ይሻለዋል። ከሚስትህ ጋር ሳለህ ከእርስዋ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት ከሌለህ ግን ሚስትን አትሻ። ብታገባም ኀጢአት አይሆንብህም፤ ድንግሊቱም ባል ብታገባ ኀጢአት አይሆንባትም፤ ያገቡ ግን ለራሳቸው ድካምን ይሻሉ፤ እኔም ይህን የምላችሁ ስለማዝንላችሁ ነው። ነገር ግን ወንድሞቻችን እንዲህ ይቀናል፤ የዚህ ዓለም ኑሮ ሁሉ ሊያልፍ ቀርቦአልና፤ አሁንም ያገቡ እንዳላገቡ ይሆናሉ። ያለቀሱ እንዳላለቀሱ ይሆናሉ፤ ደስ ያላቸውም ደስ እንዳላላቸው ይሆናሉ፤ የሸጡም እንዳልሸጡ ይሆናሉ፤ የገዙም እንዳልገዙ ይሆናሉ። የበሉ እንዳልበሉ ይሆናሉ፤ የጠጡም እንዳልጠጡ ይሆናሉ፤ የዚህ ዓለም ተድላ ሁሉ ያልፋልና። እኔስ ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ፤ ያላገባ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኘው የእግዚአብሔርን ነገር ያስባልና። ያገባ ግን ሚስቱን ደስ ሊያሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ያስባል። እንዲህ ከሆነ ግን ተለያየ፤ አግብታ የፈታች ሴትም ያላገባች ድንግልም ብትሆን ነፍስዋም ሥጋዋም ይቀደስ ዘንድ እግዚአብሔርን ታስበዋለች፤ ያገባች ግን ባልዋን ደስ ልታሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ታስባለች። ይህንም የምላችሁ እንዲጠቅማችሁ ነው፤ ላጠምዳችሁ ግን አይደለም፤ ኑሮአችሁ አንድ ወገን እንዲሆንና እግዚአብሔርን ያለመጠራጠር እንድታገለግሉት ነው እንጂ።
1 ቆሮንቶስ 7:25-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለ ደናግል፣ ከጌታ የተቀበልሁት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ምሕረት የተነሣ እንደ ታማኝ ሰው፣ ምክሬን እሰጣለሁ። አሁን ካለው ችግር የተነሣ ባላችሁበት ሁኔታ ብትኖሩ መልካም ይመስለኛል። አግብተህ ከሆነ መፋታትን አትሻ፤ ካላገባህም ሚስት ለማግባት አትፈልግ። ብታገባ ግን ኀጢአት አልሠራህም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኀጢአት አላደረገችም። ነገር ግን የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፤ እኔም ይህ እንዳይደርስባችሁ እወድዳለሁ። ወንድሞች ሆይ፤ ሐሳቤ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ ዐጭር ነው፤ ከእንግዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ሆነው ይኑሩ። የሚያለቅሱ እንደማያለቅሱ፣ ደስተኞች ደስ እንደማይላቸው ይሁኑ፤ ዕቃ የሚገዙም የገዙት ነገር የእነርሱ እንዳልሆነ ይቍጠሩ፤ በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም መልክ ዐላፊ ነውና። እኔስ ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወድዳለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን ደስ ለማሠኘት ስለ ጌታ ነገር ያስባል፤ ያገባ ሰው ግን ሚስቱን ደስ ለማሠኘት የዚህን ዓለም ነገር ያስባል፤ በዚህም ልቡ ተከፍሏል። ያላገባች ሴት ወይም ድንግል ስለ ጌታ ነገር ታስባለች፤ ዐላማዋም በሥጋና በመንፈስ ለጌታ መቀደስ ነው። ያገባች ሴት ግን ባሏን ደስ ለማሠኘት የዚህን ዓለም ነገር ታስባለች። ይህንም የምለው ለእናንተ የሚበጃችሁን ነገር በማሰብ እንጂ ላስጨንቃችሁ አይደለም፤ ዐላማዬም ልባችሁ ሳይከፈል በጌታ ጸንታችሁ በአግባብ እንድትኖሩ ነው።
1 ቆሮንቶስ 7:25-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ። እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ። ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር። ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል። ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።
1 ቆሮንቶስ 7:25-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስላላገቡ ሰዎች ከጌታ የተቀበልኩት ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት እምነት የሚጣልብኝ እንደ መሆኔ መጠን የራሴ ሐሳብ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው፤ አሁን ያለንበት ጊዜ የችግር ጊዜ ስለ ሆነ ሳያገቡ በብቸኝነት መኖር መልካም ይመስለኛል፤ ሆኖም ሚስት አግብተህ እንደ ሆነ ለመፍታት አትፈልግ፤ ሚስት አላገባህ እንደ ሆነ ለማግባት አትፈልግ። ነገር ግን አንተ ሚስት ብታገባ ኃጢአት ይሆንብሃል ማለት አይደለም፤ እንዲሁም አንዲት ልጃገረድ ባል ብታገባ ኃጢአት ይሆንባታል ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ የኑሮ ችግር ይገጥማቸዋል፤ የእኔም ምኞት ከዚህ ችግር እንድትድኑ ነው። ወንድሞች ሆይ! እኔ የምላችሁ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ አጥሮአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያለችው ሚስት እንደሌለችው ሆኖ ይኑሩ። ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌሉአቸው ሆነው ይኑር። የሚያዝኑም እንደማያዝኑ፥ የሚደሰቱ እንደማይደሰቱ ሆነው ይኑሩ፤ ዕቃ የሚገዙ፥ ምንም ዕቃ እንደሌላቸው አድርገው ይቊጠሩ። በዚህ ዓለም ሀብት የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ሆነው ይኑሩ፤ የአሁኑ ዓለም ሁኔታ አላፊ ነው። ስለዚህ በምንም ሐሳብ ሳትጨነቁ እንድትኖሩ እወዳለሁ፤ ሚስት ያላገባ ሰው ጌታ የሚደሰትበትን ነገር ስለሚፈልግ አሳቡ የሚያተኲረው፥ ጌታን በሚመለከት ሥራ ላይ ነው። ሚስት ያገባ ሰው ግን የሚያስበው ስለዚህ ዓለም ነገርና ሚስቱንም የሚያስደስትበትን ነገር ነው። በዚህ ሁኔታ ሐሳቡ በሁለት ተከፍሎአል ማለት ነው። እንዲሁም ባል ያላገባች ሴት ወይም ልጃገረድ በሥጋዋና በነፍስዋ ተቀድሳ የጌታ ለመሆን ስለምትፈልግ ሐሳቧ የሚያተኲረው ጌታን በሚመለከት ሥራ ነው። ያገባች ሴት ግን ባልዋን ለማስደሰት ስለምትፈልግ የምታስበው የዓለምን ነገር ነው። እኔ ይህን የምላችሁ በወጥመድ ውስጥ ገብታችሁ እንድትቸገሩ ብዬ ሳይሆን እንድትጠቀሙ ብዬ ነው፤ ምኞቴም እናንተ በተገቢው ሁኔታ እንድትኖሩና አሳባችሁ ሳይባክን በሙሉ ልባችሁ ጌታን እንድታገለግሉ ነው።
1 ቆሮንቶስ 7:25-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደናግልን በተመለከተ የጌታ ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት የታመንሁ እሆን ዘንድ ምክሬን እለግሳችሀለሁ፤ እንግዲህ አሁን ላለንበት ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። ሚስት አግብተህ እንደሆንህ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት አላገባህ እንደሆንህ ለማግባት አትፈልግ። ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይገጥማቸዋል፤ እኔም ከዚያ ባስጣልኳችሁ ነበር። ዳሩ ግን ወንድሞች ሆይ! ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። ነገር ግን ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንደሚያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፤ ልቡም ተከፍሎአል። ያላገባች ሴትና ድንግል በሰውነት በመንፈስም እንድትቀደስ የጌታን ነገር ታስባለች፤ ያገባች ግን ባሏን እንዴት ደስ እንደምታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአግባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም ለጌታ በጽናት እንድታገለግሉ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።