1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:25-35

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:25-35 መቅካእኤ

ደናግልን በተመለከተ የጌታ ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት የታመንሁ እሆን ዘንድ ምክሬን እለግሳችሀለሁ፤ እንግዲህ አሁን ላለንበት ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። ሚስት አግብተህ እንደሆንህ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት አላገባህ እንደሆንህ ለማግባት አትፈልግ። ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይገጥማቸዋል፤ እኔም ከዚያ ባስጣልኳችሁ ነበር። ዳሩ ግን ወንድሞች ሆይ! ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። ነገር ግን ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንደሚያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፤ ልቡም ተከፍሎአል። ያላገባች ሴትና ድንግል በሰውነት በመንፈስም እንድትቀደስ የጌታን ነገር ታስባለች፤ ያገባች ግን ባሏን እንዴት ደስ እንደምታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአግባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም ለጌታ በጽናት እንድታገለግሉ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።