1 ቆሮንቶስ 6:1-11
1 ቆሮንቶስ 6:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ በሚነቅፉ ሰዎች ዘንድ ልትከራከሩ አትድፈሩ፤ ከጓደኛው ጋር በዐመፀኞች ዘንድ ሊከራከር የሚችል አለን? በደጋጎች ዘንድ አይደለምን? ከባልንጀራው ጋር ክርክር ያለው ቢኖርም በቅዱሳን ዘንድ ይከራከር፤ በሚነቅፉና በዐመፀኞች ዘንድ ግን አይደለም። ቅዱሳን ሰውን ሁሉ እንደሚዳኙ አታውቁምን? እናንተ ሰውን ሁሉ የምትዳኙ ከሆናችሁ ይህን ትንሹን ነገር ልትዳኙ አይገባችሁምን? የዚህንስ ዓለም ዳኝነት ተዉትና በመላእክት ስንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? ነገር ግን የዚህ ዓለም ክርክር ያላቸው ሰዎች ቢኖሩ በቤተ ክርስቲያን የተሾሙ የበታች ወንድሞች ይስሙአቸው። ይህንም የምላችሁ ስዘልፋችሁ ነው፤ እንግዲህ ከመካከላቸሁ ወንድማማቾችን ከወንድሞቻቸው ጋር ማስታረቅ የሚችል ሽማግሌ የለምን? ነገር ግን ወንድም ከወንድሙ ጋር ይካሰሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል። እንግዲህ ፀብና ክርክር ካላችሁ፥ ከመጀመሪያው ጀምሮ ውርደት እንደሚሆንባችሁ ዕወቁ፤ እንግዲያማ እንዴት አትነጠቁም? እንዴትስ አትገፉም? አሁንም ቢሆን፥ እናንተ ዐመፀኞችና ቀማኞች ናችሁ፤ እንደዚህም ወንድሞቻችሁን ትበድላላችሁ። ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አያስቱአችሁ፤ ሴሰኞች፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ፥ ወይም አመንዝራዎች፥ ወይም ቀላጮች፥ ወይም በወንድ ላይ ዝሙትን የሚሠሩ፥ የሚሠሩባቸውም ቢሆኑ፤ ሌቦች፥ ወይም ቀማኞች፥ ወይም ሰካሮች፥ ወይም ተሳዳቢዎች፥ ወይም ነጣቂዎች፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱአትም። እንግዲህ እናንተ እንዲህ ስትሆኑ እነማን ናችሁ? ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋልም።
1 ቆሮንቶስ 6:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከመካከላችሁ አንድ ሰው ከሌላው ጋራ ሙግት ቢኖረው፣ ጕዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፈንታ እንዴት ደፍሮ በዐመፀኞች ፊት ለመፋረድ ያቀርባል? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ እንግዲያው፣ በትንሹ ነገር ላይ ለመፍረድ አትበቁምን? በምድራዊ ሕይወት ጕዳይ ቀርቶ፣ በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ እንዲህ ያለ ጕዳይ ሲያጋጥማችሁ፣ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጅ አድርጋችሁ ሹሟ! ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ብዬ ነው። ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ለመፍረድ የሚበቃ ጠቢብ ሰው በመካከላችሁ የለምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ለመክሰስ ፍርድ ቤት ይሄዳል፤ ያውም በማያምኑ ሰዎች ፊት! እንግዲህ በመካከላችሁ መካሰስ መኖሩ ራሱ ውድቀታችሁን ያሳያል። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? እናንተ ግን ራሳችሁ ትበድላላችሁ፤ ታታልላላችሁም፤ ያውም እኮ ወንድሞቻችሁን። ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ወይም ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።
1 ቆሮንቶስ 6:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን? አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን። ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።
1 ቆሮንቶስ 6:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእናንተ አንዱ ክርስቲያን ከሆነው ወንድሙ ጋር ቢጣላ ጉዳዩን ክርስቲያኖች በፍርድ እንዲያዩለት በማድረግ ፈንታ ለክስ ወደ አሕዛብ የፍርድ ሸንጎ ለመሄድ እንዴት ይደፍራል? የእግዚአብሔር ሰዎች በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? ታዲያ፥ በዓለም ላይ የምትፈርዱ ሲሆን በዚህ በትንሽ ነገር ላይ መፍረድ ያቅታችኋልን? በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? ታዲያ፥ በዚህ ዓለም ነገሮች ላይ በይበልጥ መፍረድ እንዴት አንችልም? እንግዲህ እርስ በርሳችሁ ብትጣሉ ከክርስቲያናዊ ማኅበር ውጪ በሆኑትና በተናቁት ሰዎች ፊት ጉዳያችሁን እንዴት ታቀርባላችሁ? ይህን የምለው እንድታፍሩ ብዬ ነው፤ ኧረ ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ውሳኔ ለመስጠት የሚችል አስተዋይ ሽማግሌ አይገኝምን? ታዲያ፥ አንድ ክርስቲያን ሌላውን ክርስቲያን ከሶ ወደ አሕዛብ ፍርድ ቤት መውሰድ ይገባዋልን? እንዲያውም እርስ በርሳችሁ ተካሳችሁ መሟገት ራሱ ለእናንተ ውርደት ነው፤ ይልቅስ እናንተ ብትበደሉ አይሻልምን? እንዲሁም እናንተ ብትታለሉ አይሻልምን? እናንተ ግን ወንድሞቻችሁ በሆኑት ክርስቲያኖች ላይ እንኳ በደልና ማታለል ትፈጽማላችሁ። ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ ታውቁ የለምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፥ ወይም ጣዖት አምላኪዎች፥ ወይም አመንዝራዎች፥ ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፥ ወይም ሌቦች፥ ወይም ስግብግቦች፥ ወይም ሰካራሞች፥ ወይም የሰው ስም አጥፊዎች፥ ወይም ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቻችሁ እንዲሁ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ከኃጢአት ታጥባችኋል፤ ለእግዚአብሔር የተለየ ቅዱስ ሕዝብ ሆናችኋል፤ ጸድቃችኋልም።
1 ቆሮንቶስ 6:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ጥል ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በአሕዛብ ፊት ሊፋረድ እንዴት ይደፍራል? ወይስ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፥ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ ያቅታችኋልን? እለታዊው የሕይወት ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ ለዚህ መሰል ጉዳይ ፍርድ ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ እንዴት ታስቀምጣላችሁ? እንድታፍሩ ስል ይህን እላለሁ። ኧረ ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል! እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በእርስ ሙግት በመካከላችሁ መፍጠር ለእናንተ ሽንፈት ነው። ይልቅስ ብትበደሉ አይሻልምን? እንዲሁም ብትታለሉ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ፤ ታታልሉማላችሁ፤ ያውም ወንድሞቻችሁን። ወይስ ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አትሳሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፥ ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።