ከእናንተ አንዱ ክርስቲያን ከሆነው ወንድሙ ጋር ቢጣላ ጉዳዩን ክርስቲያኖች በፍርድ እንዲያዩለት በማድረግ ፈንታ ለክስ ወደ አሕዛብ የፍርድ ሸንጎ ለመሄድ እንዴት ይደፍራል? የእግዚአብሔር ሰዎች በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? ታዲያ፥ በዓለም ላይ የምትፈርዱ ሲሆን በዚህ በትንሽ ነገር ላይ መፍረድ ያቅታችኋልን? በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? ታዲያ፥ በዚህ ዓለም ነገሮች ላይ በይበልጥ መፍረድ እንዴት አንችልም? እንግዲህ እርስ በርሳችሁ ብትጣሉ ከክርስቲያናዊ ማኅበር ውጪ በሆኑትና በተናቁት ሰዎች ፊት ጉዳያችሁን እንዴት ታቀርባላችሁ? ይህን የምለው እንድታፍሩ ብዬ ነው፤ ኧረ ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ውሳኔ ለመስጠት የሚችል አስተዋይ ሽማግሌ አይገኝምን? ታዲያ፥ አንድ ክርስቲያን ሌላውን ክርስቲያን ከሶ ወደ አሕዛብ ፍርድ ቤት መውሰድ ይገባዋልን? እንዲያውም እርስ በርሳችሁ ተካሳችሁ መሟገት ራሱ ለእናንተ ውርደት ነው፤ ይልቅስ እናንተ ብትበደሉ አይሻልምን? እንዲሁም እናንተ ብትታለሉ አይሻልምን? እናንተ ግን ወንድሞቻችሁ በሆኑት ክርስቲያኖች ላይ እንኳ በደልና ማታለል ትፈጽማላችሁ። ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ ታውቁ የለምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፥ ወይም ጣዖት አምላኪዎች፥ ወይም አመንዝራዎች፥ ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፥ ወይም ሌቦች፥ ወይም ስግብግቦች፥ ወይም ሰካራሞች፥ ወይም የሰው ስም አጥፊዎች፥ ወይም ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቻችሁ እንዲሁ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ከኃጢአት ታጥባችኋል፤ ለእግዚአብሔር የተለየ ቅዱስ ሕዝብ ሆናችኋል፤ ጸድቃችኋልም።
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች