1 ቆሮንቶስ 6:1-11

1 ቆሮንቶስ 6:1-11 NASV

ከመካከላችሁ አንድ ሰው ከሌላው ጋራ ሙግት ቢኖረው፣ ጕዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፈንታ እንዴት ደፍሮ በዐመፀኞች ፊት ለመፋረድ ያቀርባል? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ እንግዲያው፣ በትንሹ ነገር ላይ ለመፍረድ አትበቁምን? በምድራዊ ሕይወት ጕዳይ ቀርቶ፣ በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ እንዲህ ያለ ጕዳይ ሲያጋጥማችሁ፣ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጅ አድርጋችሁ ሹሟ! ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ብዬ ነው። ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ለመፍረድ የሚበቃ ጠቢብ ሰው በመካከላችሁ የለምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ለመክሰስ ፍርድ ቤት ይሄዳል፤ ያውም በማያምኑ ሰዎች ፊት! እንግዲህ በመካከላችሁ መካሰስ መኖሩ ራሱ ውድቀታችሁን ያሳያል። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? እናንተ ግን ራሳችሁ ትበድላላችሁ፤ ታታልላላችሁም፤ ያውም እኮ ወንድሞቻችሁን። ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ወይም ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።