1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6:1-11

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6:1-11 መቅካእኤ

ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ጥል ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በአሕዛብ ፊት ሊፋረድ እንዴት ይደፍራል? ወይስ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፥ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ ያቅታችኋልን? እለታዊው የሕይወት ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ ለዚህ መሰል ጉዳይ ፍርድ ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ እንዴት ታስቀምጣላችሁ? እንድታፍሩ ስል ይህን እላለሁ። ኧረ ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል! እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በእርስ ሙግት በመካከላችሁ መፍጠር ለእናንተ ሽንፈት ነው። ይልቅስ ብትበደሉ አይሻልምን? እንዲሁም ብትታለሉ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ፤ ታታልሉማላችሁ፤ ያውም ወንድሞቻችሁን። ወይስ ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አትሳሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፥ ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።