1 ቆሮንቶስ 2:9-12
1 ቆሮንቶስ 2:9-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን መጽሐፍ፥ “ዐይን ያላየው፥ ጆሮም ያልሰማው፥ በሰውም ልቡና ያልታሰበ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ነው።” ብሎ የለምን? ለእኛም እግዚአብሔር በመንፈሱ ገለጠልን፤ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምሥጢሩን ያውቃልና። በሰው ልቡና ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? በእርሱ ያለችው ነፍሱ ናት እንጂ፤ እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ የለም። እኛ የዚህን ዓለም መንፈስ የተቀበልን አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሚሆነውን መንፈስ ተቀበልን።
1 ቆሮንቶስ 2:9-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይሁን እንጂ፣ እንደ ተጻፈው፣ “ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን፣ እግዚአብሔር ለሚወድዱት አዘጋጅቷል፤” እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በስተቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በስተቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው።
1 ቆሮንቶስ 2:9-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።
1 ቆሮንቶስ 2:9-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይሁን እንጂ መጽሐፍ፥ “የሰው ዐይን ያላየውን፥ የሰው ጆሮ ያልሰማውን፥ የሰው ልብ ያላሰበውን፥ እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል” ይላል። ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካይነት ምሥጢሩን ገልጦልናል፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ነገር ይመረምራል። ስለ ሰው የሆነ እንደ ሆነ ከገዛ ራሱ መንፈስ በቀር በእርሱ ያለውን ሐሳብ የሚያውቅ ማን ነው? እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ነገር እንድናውቅ የእግዚአብሔርን መንፈስ እንጂ የዚህን ዓለም መንፈስ አልተቀበልንም።
1 ቆሮንቶስ 2:9-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን እንደተጻፈው፥ “ዐይን ያላየውን፤ ጆሮም ያልሰማው፤ በሰውም ልብ ያልታሰበው፤ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው፤” ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። መንፈስ፥ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር፥ ሁሉን ይመረምራልና። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር የሰውን ነገር የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን ነገር ማንም አያውቅም። እኛ ግን፥ እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር በነፃ የተሰጠንን፥ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።