የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2

2
ስለተሰቀለው ክርስቶስ ማስተማር
1ወንድሞች ሆይ! እኔ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ የእግዚአብሔርን ምስጢር በቃላት መራቀቅ ወይም ጥበብ ለእናንተ ለማወጅ አልመጣሁም። 2በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር፥ እርሱም እንደ ተሰቀለ፥ ሌላ ነገር ላለማወቅ ወስኜ ነበርና። 3#የሐዋ. 18፥9።እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤ 4ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ 5ይህም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰዎች ጥበብ እንዳይሆን ነው።
ስለ እውነተኛው ጥበብ
6በዐዋቂዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚህን ዓለም ወይም መጨረሻቸው ጥፋት የሚሆነውን የዚህን ዓለም ገዢዎች ጥበብ አይደለም፤ 7ነገር ግን፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር ተሰውሮም የነበረውን እንናገራለን። 8#ባሮክ 3፥14-17።ከዚችም ዓለም ገዢዎች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ፥ አላወቀም፤ ዐውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ 9#ኢሳ. 64፥4፤ ሲራ. 1፥9፤10።ነገር ግን እንደተጻፈው፥
“ዐይን ያላየውን፤
ጆሮም ያልሰማው፤
በሰውም ልብ ያልታሰበው፤
እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው፤”
10ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። መንፈስ፥ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር፥ ሁሉን ይመረምራልና። 11በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር የሰውን ነገር የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን ነገር ማንም አያውቅም። 12እኛ ግን፥ እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር በነፃ የተሰጠንን፥ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 13ይህን ደግሞ፥ መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን፥ መንፈስ በሚያስተምረን ቃል እንናገራለን እንጂ ከሰው ጥበብ በሚገኝ ቃል አይደለም።
14ፍጥረታዊ ሰው ግን የእግዚአብሔርን መንፈስ ነገር አይቀበለውም፤ ይህ ለእርሱ ሞኝነት ነው፥ ምክንያቱም በመንፈስ የሚመረመር ነውና፥ ሊያውቀው አይችልም። 15መንፈሳዊ ሰው ሁሉን ይመረምራል፤ እሱ ግን በማንም አይመረመርም። 16#ኢሳ. 40፥13።ሊመክረውስ የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልቦና አለን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ