1 ቆሮንቶስ 2:6-15
1 ቆሮንቶስ 2:6-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለዐዋቆች ጥበብን እንነግራቸዋለን፤ ነገር ግን የዚህን ዓለም ጥበብ ወይም ያልፉ ዘንድ ያላቸውን የዚህን ዓለም ሹሞች ጥበብ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔር ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። የዚህ ዓለም ሹሞችም አላወቁትም፤ ይህንስ ቢያውቁ ኑሮ የክብር ባለቤትን ባልሰቀሉትም ነበር። ነገር ግን መጽሐፍ፥ “ዐይን ያላየው፥ ጆሮም ያልሰማው፥ በሰውም ልቡና ያልታሰበ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ነው።” ብሎ የለምን? ለእኛም እግዚአብሔር በመንፈሱ ገለጠልን፤ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምሥጢሩን ያውቃልና። በሰው ልቡና ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? በእርሱ ያለችው ነፍሱ ናት እንጂ፤ እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ የለም። እኛ የዚህን ዓለም መንፈስ የተቀበልን አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሚሆነውን መንፈስ ተቀበልን። ይህም ትምህርታችን ከሰው የተገኘ ትምህርት አይደለም፤ የአነጋገር ጥበብም አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ የገለጸው ትምህርት ነው እንጂ፤ መንፈሳዊ ጥበብም ከመንፈስ ቅዱስ የሚሆነውን መርምረው ለሚያውቁ ለመንፈሳውያን ነው። ለሥጋዊ ሰው ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ይመስለዋልና፥ አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቅ አይችልም። መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል፤ እርሱን ግን የሚመረምረው የለም።
1 ቆሮንቶስ 2:6-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በበሰሉ ሰዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚህችን ዓለም ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚህችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም። ነገር ግን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው። ከዚህ ዓለም ገዦች አንዳቸውም ይህን ጥበብ አልተረዱትም፤ ቢረዱትማ ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር። ይሁን እንጂ፣ እንደ ተጻፈው፣ “ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን፣ እግዚአብሔር ለሚወድዱት አዘጋጅቷል፤” እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በስተቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በስተቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው። እኛ የምንናገረው ይህን ነው፤ ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል ሳይሆን፣ ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን፤ መንፈሳዊ እውነትንም የምንገልጸው በመንፈሳዊ ቃል ነው። መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ የሆነውን ነገር ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ነገር ለእርሱ ሞኝነት ነው፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ፣ ሊረዳው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።
1 ቆሮንቶስ 2:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።
1 ቆሮንቶስ 2:6-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ነገር ግን በመንፈሳዊ ሕይወት ለበሰሉት በጥበብ ቃል እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የምንናገረው የዚህን ዓለም ጥበብ ወይም መጨረሻቸው ጥፋት የሚሆነውን የዚህን ዓለም ገዢዎች ጥበብ አይደለም። እኛ የምንናገረው ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን ያዘጋጀውንና ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምሥጢር ጥበብ ነው። ከዚህ ዓለም ገዢዎች መካከል ይህን ጥበብ ያወቀ ማንም የለም፤ ዐውቀውትስ ቢሆን ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ፥ “የሰው ዐይን ያላየውን፥ የሰው ጆሮ ያልሰማውን፥ የሰው ልብ ያላሰበውን፥ እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል” ይላል። ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካይነት ምሥጢሩን ገልጦልናል፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ነገር ይመረምራል። ስለ ሰው የሆነ እንደ ሆነ ከገዛ ራሱ መንፈስ በቀር በእርሱ ያለውን ሐሳብ የሚያውቅ ማን ነው? እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ነገር እንድናውቅ የእግዚአብሔርን መንፈስ እንጂ የዚህን ዓለም መንፈስ አልተቀበልንም። ስለዚህ እኛ መንፈሳዊውን ነገር ለመንፈሳውያን ሰዎች የምናስተምረው ከሰው በሚገኘው ጥበብ ሳይሆን ከእግዚአብሔር መንፈስ በሚገኘው ጥበብ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ የሌለው ሥጋዊ ሰው ግን ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚሰጠውን ስጦታ መቀበል አይችልም፤ የስጦታው ታላቅነት የሚመረመረው በእግዚአብሔር መንፈስ አማካይነት ስለ ሆነ ሊያስተውለው አይችልም፤ እንዲያውም ይህ ለእርሱ ሞኝነት መስሎ ይታየዋል። የእግዚአብሔር መንፈስ ያለው ግን ሁሉን ነገር መመርመር ይችላል፤ እርሱ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።
1 ቆሮንቶስ 2:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዐዋቂዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚህን ዓለም ወይም መጨረሻቸው ጥፋት የሚሆነውን የዚህን ዓለም ገዢዎች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር ተሰውሮም የነበረውን እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዢዎች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ፥ አላወቀም፤ ዐውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን እንደተጻፈው፥ “ዐይን ያላየውን፤ ጆሮም ያልሰማው፤ በሰውም ልብ ያልታሰበው፤ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው፤” ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። መንፈስ፥ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር፥ ሁሉን ይመረምራልና። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር የሰውን ነገር የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን ነገር ማንም አያውቅም። እኛ ግን፥ እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር በነፃ የተሰጠንን፥ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። ይህን ደግሞ፥ መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን፥ መንፈስ በሚያስተምረን ቃል እንናገራለን እንጂ ከሰው ጥበብ በሚገኝ ቃል አይደለም። ፍጥረታዊ ሰው ግን የእግዚአብሔርን መንፈስ ነገር አይቀበለውም፤ ይህ ለእርሱ ሞኝነት ነው፥ ምክንያቱም በመንፈስ የሚመረመር ነውና፥ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ሁሉን ይመረምራል፤ እሱ ግን በማንም አይመረመርም።