1 ቆሮንቶስ 16:1-9
1 ቆሮንቶስ 16:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሁን ደግሞ ለቅዱሳን ስለሚደረገው ገንዘብ ማሰባሰብ፤ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት አድርጉ። ገንዘብ ማሰባሰብ የሚደረገው እኔ በምመጣበት ጊዜ እንዳይሆን፣ ከእናንተ እያንዳንዱ እንደ ገቢው መጠን በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እየለየ ያስቀምጥ። በምመጣበት ጊዜ እናንተ ለመረጣችኋቸው ሰዎች የመሸኛ ደብዳቤ ሰጥቼ ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ። የእኔ መሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ ዐብረውኝ ይሄዳሉ። በመቄዶንያ በኩል ማለፌ ስለማይቀር፣ መቄዶንያ ከደረስሁ በኋላ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ወደምሄድበት ወደ ማንኛውም ስፍራ በጕዞዬ እንድትረዱኝ፣ እናንተ ዘንድ እቈይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋራ እሰነብት ይሆናል። አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ ጌታ ቢፈቅድ ረዘም ላለ ጊዜ እናንተ ዘንድ ለመሰንበት ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን እስከ በዓለ ዐምሳ በኤፌሶን እቈያለሁ፤ ምክንያቱም ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤ ብዙ ተቃዋሚዎችም አሉብኝ።
1 ቆሮንቶስ 16:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ለምእመናን ስለሚደረገው የገንዘብ መዋጮ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያን በሰጠሁት መመሪያ መሠረት እናንተም እንዲሁ አድርጉ። እኔ በምመጣበት ጊዜ የገንዘብ መዋጮ እንዳይደረግ በየሳምንቱ እሑድ ከእናንተ እያንዳንዱ በሚያገኘው ገቢ መጠን እያዋጣ ለይቶ ያስቀምጥ። እኔ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ እናንተ የምትመርጥዋቸውን ሰዎች ያዋጣችሁትን ገንዘብ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱ ከመሸኛ ደብዳቤ ጋር እልካቸዋለሁ። የእኔም መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ አብረውኝ ይሄዳሉ። በመቄዶንያ በኩል ለመሄድ ስለ ዐቀድኩ በዚያ ሳልፍ እግረ መንገዴን ወደ እናንተ እመጣለሁ። ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ ለጒዞዬ የሚሆነኝን ርዳታ እንድታደርጉልኝ ምናልባት እናንተ ዘንድ እቈይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር አሳልፍ ይሆናል፤ አሁን ሳልፍ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ የጌታ ፈቃድ ቢሆን ጥቂት ረዘም ያለ ጊዜ ከእናንተ ጋር ለመቈየት ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን እስከ ጰንጠቆስጤ በዓል በኤፌሶን እቈያለሁ። ብዙ ሥራ ያለበት ሰፊ በር ተከፍቶልኛል፤ ተቃዋሚዎች ግን ብዙዎች ናቸው።
1 ቆሮንቶስ 16:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለቅዱሳን ስለሚደረገው አስተዋፅኦ በገላትያ ላሉት ምእመናን እንደ ደነገግሁት እናንተም እንዲሁ አድርጉ። እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያንጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ ሰው ሁሉ በየሳምንቱ እሑድ የተቻለውን ያወጣጣ፤ ያገኘውንም በቤቱ ይጠብቅ። በመጣሁ ጊዜም ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ የመረጣችኋቸውን ሰዎች መልእክቴን ጨምሬ እልካቸዋለሁ። ለመሄድ ቢቻለኝ ግን እኔ ራሴ እሄዳለሁና፥ እነርሱም አብረውኝ ይሄዳሉ። መቄዶንያም ደርሼ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመቄዶንያ በኩል አልፋለሁና። እናንተም ወደምሄድበት ትሸኙኝ ዘንድ ምንአልባት የሆነውን ቀን ያህል በእናንተ ዘንድ እቈይ፥ ወይም እከርም ይሆናል። አሁን እግረ መንገዴን ላያችሁ አልሻም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የፈቀደ እንደ ሆነ የሆነውን ቀን ያህል በእናንተ ዘንድ እንደምቈይ ተስፋ አደርጋለሁ። እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቈያለሁ። ሥራ የሞላበት ታላቅ በር ተከፍቶልኛልና፤ ነገር ግን ብዙዎች ተቃዋሚዎች አሉ።
1 ቆሮንቶስ 16:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለቅዱሳንም ገንዘብን ስለ ማዋጣት፥ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያን ጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ። ስመጣም ማናቸውም ቢሆኑ የታመኑ የሚመስሉአችሁ ሰዎች ቸርነታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ ደብዳቤ ሰጥቼ እልካቸዋለሁ፤ እኔ ደግሞ ልሄድ የሚገባኝ ብሆን ከእኔ ጋር አብረው ይሄዳሉ። በመቄዶንያም ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመቄዶንያ አድርጌ አልፋለሁና፤ እናንተም ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ምናልባት በእናንተ ዘንድ እቆይ ወይም እከርም ይሆናል። አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጎበኛችሁ አልወድምና፤ ጌታ ቢፈቅደው የሆነውን ዘመን በእናንተ ዘንድ ልሰነብት ተስፋ አደርጋለሁና። በኤፌሶን ግን እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ እሰነብታለሁ። ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው።
1 ቆሮንቶስ 16:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሁን ደግሞ ለቅዱሳን የሚደረገውን የገንዘብ መዋጮ በተመለከተ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በሰጠሁት መመሪያ መሠረት አድርጉ። እኔ በምመጣበት ጊዜ የገንዘብ መዋጮ እንዳይደረግ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ እንደገቢው መጠን በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እየለየ ያስቀምጥ፤ እኔ ስመጣ እናንተ ለመረጣችኋቸው ሰዎች የመሸኛ ደብዳቤ ሰጥቼ ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ። የእኔ መሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ አብረውኝ ይሄዳሉ። በመቄዶንያ በኩል ለመሄድ ስላቀድኩ በዚያ ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጉዞዬ እንድትረዱኝ፥ እናንተ ጋር እቆይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር እሰነብት ይሆናል። አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ ጌታ ቢፈቅድ ረዘም ላለ ጊዜ እናንተ ዘንድ ለመሰንበት ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቆያለሁ፤ ምክንያቱም ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤ ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው።