1 ቆሮንቶስ 10:14-33

1 ቆሮንቶስ 10:14-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወን​ድ​ሞች! አሁ​ንም ጣዖት ከማ​ም​ለክ ሽሹ። ለዐ​ዋ​ቂ​ዎች እን​ደ​ሚ​ነ​ገር እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ፤ ትክ​ክ​ለ​ኛ​ው​ንም እና​ንተ ራሳ​ችሁ ፍረዱ። ይህ የም​ን​ባ​ር​ከው የበ​ረ​ከት ጽዋ ከክ​ር​ስ​ቶስ ደም ጋር አንድ አይ​ደ​ለ​ምን? የም​ን​ፈ​ት​ተው ይህስ ኅብ​ስት ከክ​ር​ስ​ቶስ ሥጋ ጋር አንድ አይ​ደ​ለ​ምን? ኅብ​ስቱ አንድ እንደ ሆነ እን​ዲሁ እኛም ብዙ​ዎች ስን​ሆን አንድ አካል ነን፤ ሁላ​ችን ከአ​ንድ ኅብ​ስት እን​ቀ​በ​ላ​ለ​ንና። እስ​ራ​ኤል ዘሥ​ጋን ተመ​ል​ከቱ፤ መሥ​ዋ​ዕ​ቱን ይበ​ላሉ፤ ከመ​ሠ​ዊ​ያ​ውም ጋር አንድ ይሆኑ አል​ነ​በ​ረ​ምን? እን​ግ​ዲህ ምን እን​ላ​ለን? ለጣ​ዖ​ታት የሚ​ሠዋ መሥ​ዋ​ዕት ከንቱ ነው፤ ጣዖ​ቶ​ቻ​ቸ​ውም ከንቱ ናቸው። አሕ​ዛ​ብም የሚ​ሠዉ ለአ​ጋ​ን​ንት ነው እንጂ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አይ​ደ​ለም፤ ነገር ግን የአ​ጋ​ን​ንት ተባ​ባ​ሪ​ዎች እን​ድ​ት​ሆኑ አል​ፈ​ቅ​ድ​ላ​ች​ሁም። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ጽዋና የአ​ጋ​ን​ን​ትን ጽዋ አንድ አድ​ር​ጋ​ችሁ መጠ​ጣት አት​ች​ሉም፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ማዕ​ድና የአ​ጋ​ን​ን​ት​ንም ማዕድ በአ​ን​ድ​ነት ልት​በሉ አት​ች​ሉም። እን​ግ​ዲህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እና​ስ​ቀ​ና​ውን? በውኑ እኛ ከእ​ርሱ እን​በ​ረ​ታ​ለን? ሁሉ ተፈ​ቅ​ዶ​ል​ኛል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚ​ጠ​ቅም አይ​ደ​ለም፤ ሁሉ ተፈ​ቅ​ዶ​ል​ኛል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚ​ያ​ንጽ አይ​ደ​ለም። ለባ​ል​ን​ጀ​ራ​ችሁ እንጂ ለራ​ሳ​ችሁ አታ​ድሉ። ደግ​ሞም በሥጋ ገበያ የሚ​ሸ​ጡ​ትን ሁሉ ከሕ​ሊና የተ​ነሣ ሳት​መ​ራ​መሩ ብሉ። “ምድር በመ​ላዋ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ናትና።” ያላ​መነ ሰው ቢጠ​ራ​ችሁ፥ ልት​ሄ​ዱም ብት​ወዱ ያቀ​ረ​ቡ​ላ​ች​ሁን ሁሉ ከሕ​ሊና የተ​ነሣ ሳት​መ​ራ​መሩ ብሉ። እን​ግ​ዲህ “ይህ ለጣ​ዖት የተ​ሠዋ ነው” ያላ​ችሁ ቢኖር ግን፥ ስለ ነገ​ራ​ች​ሁና ባል​ን​ጀ​ራ​ች​ሁም የሚ​ጠ​ራ​ጠር ስለ​ሆነ አት​ብሉ። ነጻ​ነ​ታ​ች​ሁን እን​ዳ​ይ​ነ​ቅ​ፉ​አት አስ​ረ​ድ​ተ​ዋ​ች​ኋ​ልና። በጸጋ ብበላ ግን በነ​ገሩ ስለ​ማ​መ​ሰ​ግን ለምን ይነ​ቅ​ፉ​ኛል። ብት​በ​ሉም፥ ብት​ጠ​ጡም የም​ታ​ደ​ር​ጉ​ትን ሁሉ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ክብር አድ​ር​ጉት። ለአ​ይ​ሁ​ድም፥ ለአ​ረ​ማ​ው​ያ​ንም፥ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤተ ክር​ስ​ቲ​ያ​ንም ያለ ማሰ​ና​ከል አር​አያ ሁኑ​አ​ቸው። እኔም ሁሉን በሁሉ ነገር ደስ እን​ዳ​ሰኝ ይድኑ ዘንድ የብ​ዙ​ዎ​ችን ተድላ እሻ​ለሁ እንጂ የራ​ሴን ተድላ የምሻ አይ​ደ​ለ​ሁ​ምና።

1 ቆሮንቶስ 10:14-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። ይህን የምናገረው አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ ስለምናገረው ነገር እናንተው ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋራ ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋራ ኅብረት ያለው አይደለምን? እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። እስኪ የእስራኤልን ሕዝብ አስቡ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋራ ኅብረት አልነበራቸውምን? ታዲያ፣ ለጣዖት የተሠዋ ነገርም ሆነ ጣዖቱ ራሱ ዋጋ ያለው ነገር ነው ማለቴ ነውን? አይደለም፤ አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ከአጋንንት ጋራ እንድትተባበሩም አልሻም። የጌታን ጽዋና፣ የአጋንንትን ጽዋ በአንድ ላይ መጠጣት አትችሉም፤ ከጌታ ማእድና ከአጋንንት ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም። ጌታን እናስቀናውን? በብርታትስ ከርሱ እንበልጣለንን? “ሁሉ ነገር ተፈቅዷል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉም ነገር ተፈቅዷል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አያንጽም። እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ። በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ፣ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ “ምድርና በርሷ ያለው ሁሉ የጌታ ነውና።” የማያምን ሰው ጋብዟችሁ ለመሄድ ብትፈልጉ በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ የቀረበላችሁን ሁሉ ብሉ። ነገር ግን አንዱ፣ “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ፣ ይህን ስለ ነገራችሁ ሰውና ለኅሊናችሁ ስትሉ አትብሉ። ይህን የምለውም ስለዚያ ሰው ኅሊና እንጂ ስለ አንተ አይደለም፤ ነጻነቴስ በሌላ ሰው ኅሊና ለምን ይመዘን? ምግቡን በምስጋና የምበላ ከሆነ፣ እግዚአብሔርን ባመሰገንሁበት ነገር ለምን እወቀሣለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። ለአይሁድም ሆነ ለግሪኮች ወይም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መሰናክል አትሁኑ፤ እኔ ሰውን ሁሉ በማንኛውም ረገድ ለማስደሰት እንደምጥር እናንተም እንዲሁ አድርጉ፤ ብዙዎችም ይድኑ ዘንድ፣ ለራሴ የሚጠቅመውን ሳይሆን ለእነርሱ የሚጠቅመውን እሻለሁና።

1 ቆሮንቶስ 10:14-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው እላለሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ። በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤ ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነውና። ከማያምኑ ሰዎች አንዱም ቢጠራችሁ ልትሄዱም ብትወዱ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ። ማንም ግን፦ ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው ቢላችሁ ከዚያ ካስታወቃችሁና ከሕሊና የተነሣ አትብሉ፤ ስለ ባልንጀራህ ሕሊና እንጂ ስለ ገዛ ሕሊናህ አልናገርም። አርነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ ኧረ ስለ ምንድር ነው? እኔም በጸጋ ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለ ምን እሰደባለሁ? እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ፥ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ።

1 ቆሮንቶስ 10:14-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እንግዲህ ወዳጆቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ራቁ። ይህንንም የምላችሁ አስተዋዮች በመሆናችሁ ነው፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛ እግዚአብሔርን አመስግነን የምንካፈለው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰው ኅብስት ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? ኅብስቱ አንድ በመሆኑ እኛም ከዚህ ከአንዱ ኅብስት የምንካፈል ስለ ሆንን ምንም እንኳ ብዙዎች ብንሆን አንድ አካል ነን። እስቲ የእስራኤል ሕዝብ ያደረጉትን ተመልከቱ፤ የሚቀርበውን መሥዋዕት የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን? ታዲያ ይህን ስል ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ የሚረባ ነገር ነው ማለቴ ነውን? ወይስ ጣዖት የሚረባ ነገር ነው ማለቴ ነውን? አይደለም! አሕዛብ መሥዋዕት የሚያቀርቡት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ስለዚህ እናንተ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አልፈልግም፤ የጌታን ጽዋ እየጠጣችሁ ደግሞ የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም፤ የጌታ ማእድ ተካፋዮች ሆናችሁ ደግሞ የአጋንንትን ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም፤ ታዲያ ይህን በማድረግ ጌታን እናስቀናውን? እኛ ከእርሱ ይበልጥ እንበረታለንን? ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ ነገር ጠቃሚ አይደለም፤ ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ ነገር የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም ብቻ አይፈልግ። ከኅሊናችሁ የሚነሣውን ጥርጣሬ አስወግዳችሁ ማንኛውንም በገበያ የሚሸጠውን ሥጋ ሳታመነቱ ብሉ። “ምድርና በእርስዋም ያለው ሁሉ የጌታ ነው።” ክርስቲያን ያልሆነ ሰው ቢጋብዛችሁና ግብዣውንም ብትቀበሉ የሚቀርብላችሁን ማንኛውንም ምግብ ከኅሊናችሁ የሚነሣውን ጥርጣሬ አስወግዳችሁ ሳታመነቱ ብሉ። ነገር ግን አንድ ሰው “ይህ ሥጋ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ ይህን በነገራችሁ ሰው ምክንያትና በኅሊናም ምክንያት ሥጋውን አትብሉ። ኅሊናም ስላችሁ የሰውዬውን ኅሊና ማለቴ ነው እንጂ የእናንተን ኅሊና ማለቴ አይደለም፤ ታዲያ በሌላው ሰው ኅሊና ምክንያት በእኔ ነጻነት ላይ የሚፈረደው ለምንድን ነው? እኔ እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ብበላ እግዚአብሔርን በማመሰግንበት ነገር ስለምን እወቀስበታለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማናቸውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉ። አይሁድንም ቢሆን፥ አሕዛብንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን ቢሆን፥ ማንንም አታሰናክሉ። እኔ ሁሉም እንዲድኑ የሌሎችን ጥቅም እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ ሰውን ሁሉ በማደርገው ነገር ሁሉ እንደማስደስት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።

1 ቆሮንቶስ 10:14-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ የምለውን ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ፥ የክርስቶስን ደም መካፈል አይደለምን? የምንቆርሰውስ ኀብስት፥ የክርስቶስን ሥጋ መካፈል አይደለምን? አንድ ኀብስት ስለ ሆነ፥ ሁላችን ያን አንዱን ኀብስት እንካፈላለንና፥ እኛ ብዙዎች ብንሆንም አንድ አካል ነን። በሥጋ የሆነውን እስራኤልን ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ የሚረባ ነገር ነው? ወይስ ጣዖት የሚረባ ነገር ነው? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት፤ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አልፈልግም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም አይፈልግ። ከሕሊና የተነሣ ሳትጠራጠሩ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ ምድር የጌታ ነውና፥ በእርሷ የሞላባት ሁሉ። ከማያምኑ ሰዎች አንዱ ቢጠራችሁ እናንተም ለመሄድ ብትፈልጉ ከሕሊና የተነሣ ሳትጠራጠሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ። ማንም ግን “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው፤” ቢላችሁ ይህን በነገራችሁ ሰው ምክንያትና በኅሊናም ምክንያት ሥጋውን አትብሉ፤ ስለ ሌላው ሰው ሕሊና ማለቴ እንጂ ስለ ራሳችሁ ሕሊና አይደለም። ነጻነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ ኧረ ለምንድን ነው? እኔም በምስጋና ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለምን እሰደባለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማናቸውንም ነገር ስታደርጉ፥ ሁሉን ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። ለአይሁድም ይሁን ለግሪክም እንዲሁም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ማሰናከያ አትሁኑ። እኔ ደግሞ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ ነገር ግን ብዙዎቹ እንዲጠቀሙ፥ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ ለማሰኘት የምጥረው፥ ይድኑ ዘንድ ነው።