1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10
10
ጣዖትን ማምለክ እንደማይገባ
1ወንድሞቼ ሆይ! አባቶቻችን ደመና ከበላያቸው ሆኖ ይመራቸው እንደ ነበረና ሁሉም ቀይ ባሕርን እንደ ተሻገሩ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። #ዘፀ. 13፥21-22፤ 14፥22-29። 2የሙሴ ተባባሪዎች ለመሆንም በዚህ ደመናና በዚህ ባሕር ተጠመቁ። 3ሁሉም አንድ ዐይነት መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ። #ዘፀ. 16፥35። 4ሁሉም አንድ ዐይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ የጠጡትም ይከተላቸው ከነበረው ከዚያ ከመንፈሳዊ አለት የመነጨ ነበር፤ ያም አለት ራሱ ክርስቶስ ነበር። #ዘፀ. 17፥6፤ ዘኍ. 25፥1-18። 5ይህም ሆኖ እግዚአብሔር በአብዛኞቹ አልተደሰተም፤ ስለዚህ ሬሳቸው በበረሓ ወድቆ ቀረ። #ዘኍ. 14፥29-30።
6እነርሱ ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛም ክፉ ነገር እንዳንመኝ ይህ ሁሉ ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሆኖናል። #ዘኍ. 11፥4። 7“ሰዎች ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ከመጠን በላይ ሊፈነጥዙ ተነሡ” ተብሎ ስለ እነርሱ እንደ ተጻፈው፥ እነርሱ ጣዖትን እንዳመለኩ እናንተም እንደእነርሱ ጣዖትን አታምልኩ። #ዘፀ. 32፥6። 8ከእነርሱ አንዳንዶቹ የዝሙት ኃጢአት እንደ ሠሩ እኛም የዝሙት ኃጢአት እንሥራ፤ እነርሱ ይህን በማድረጋቸው ከእነርሱ ኻያ ሦስት ሺህ ሰዎች በአንድ ቀን ሞተዋል። #ዘኍ. 25፥1-18። 9ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑትና በእባብ ተነድፈው እንደ ሞቱ እኛም ጌታን አንፈታተነው። #10፥9 ጌታ፦ አንዳንድ የጥንት ቅጂዎች “ክርስቶስ” ይላሉ። #ዘኍ. 21፥5-6። 10ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጒረመረሙና በቀሳፊው መልአክ እንደ ጠፉ እናንተም አታጒረምርሙ። #ዘኍ. 16፥41-49።
11ይህ ሁሉ ነገር የደረሰባቸው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እንዲሆን ነው፤ የተጻፈውም በዘመናት መጨረሻ ላይ ለምንገኘው ለእኛ ትምህርት እንዲሆነን ነው።
12ስለዚህ የቆመ የሚመስለው ሰው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13በሰው ከሚደርሰው ፈተና በቀር ሌላ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ከአቅማችሁ በላይ የሆነ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ በምትፈተኑበትም ጊዜ የምትታገሡበትን ኀይል በመስጠት ከፈተናው የምትወጡበትን መንገድ ያዘጋጅላችኋል።
14እንግዲህ ወዳጆቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ራቁ። 15ይህንንም የምላችሁ አስተዋዮች በመሆናችሁ ነው፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። 16እኛ እግዚአብሔርን አመስግነን የምንካፈለው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰው ኅብስት ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? #ማቴ. 26፥26-28፤ ማር. 14፥22-24፤ ሉቃ. 22፥19-20። 17ኅብስቱ አንድ በመሆኑ እኛም ከዚህ ከአንዱ ኅብስት የምንካፈል ስለ ሆንን ምንም እንኳ ብዙዎች ብንሆን አንድ አካል ነን።
18እስቲ የእስራኤል ሕዝብ ያደረጉትን ተመልከቱ፤ የሚቀርበውን መሥዋዕት የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን? #ዘሌ. 7፥6። 19ታዲያ ይህን ስል ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ የሚረባ ነገር ነው ማለቴ ነውን? ወይስ ጣዖት የሚረባ ነገር ነው ማለቴ ነውን? 20አይደለም! አሕዛብ መሥዋዕት የሚያቀርቡት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ስለዚህ እናንተ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አልፈልግም፤ #ዘዳ. 32፥17። 21የጌታን ጽዋ እየጠጣችሁ ደግሞ የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም፤ የጌታ ማእድ ተካፋዮች ሆናችሁ ደግሞ የአጋንንትን ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም፤ 22ታዲያ ይህን በማድረግ ጌታን እናስቀናውን? እኛ ከእርሱ ይበልጥ እንበረታለንን? #ዘዳ. 32፥21።
23ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ ነገር ጠቃሚ አይደለም፤ ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ ነገር የሚያንጽ አይደለም። #1ቆሮ. 6፥12። 24እያንዳንዱ ሰው የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም ብቻ አይፈልግ።
25ከኅሊናችሁ የሚነሣውን ጥርጣሬ አስወግዳችሁ ማንኛውንም በገበያ የሚሸጠውን ሥጋ ሳታመነቱ ብሉ። 26“ምድርና በእርስዋም ያለው ሁሉ የጌታ ነው።” #መዝ. 24፥1።
27ክርስቲያን ያልሆነ ሰው ቢጋብዛችሁና ግብዣውንም ብትቀበሉ የሚቀርብላችሁን ማንኛውንም ምግብ ከኅሊናችሁ የሚነሣውን ጥርጣሬ አስወግዳችሁ ሳታመነቱ ብሉ። 28ነገር ግን አንድ ሰው “ይህ ሥጋ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ ይህን በነገራችሁ ሰው ምክንያትና በኅሊናም ምክንያት ሥጋውን አትብሉ። 29ኅሊናም ስላችሁ የሰውዬውን ኅሊና ማለቴ ነው እንጂ የእናንተን ኅሊና ማለቴ አይደለም፤
ታዲያ በሌላው ሰው ኅሊና ምክንያት በእኔ ነጻነት ላይ የሚፈረደው ለምንድን ነው? 30እኔ እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ብበላ እግዚአብሔርን በማመሰግንበት ነገር ስለምን እወቀስበታለሁ?
31እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማናቸውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉ። 32አይሁድንም ቢሆን፥ አሕዛብንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን ቢሆን፥ ማንንም አታሰናክሉ። 33እኔ ሁሉም እንዲድኑ የሌሎችን ጥቅም እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ ሰውን ሁሉ በማደርገው ነገር ሁሉ እንደማስደስት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።
Currently Selected:
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997