የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11

11
1እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ። #1ቆሮ. 4፥16፤ ፊል. 3፥17።
የአምልኮ ሥነ ሥርዓት
2ዘወትር ስለምታስታውሱኝና የሰጠኋችሁንም ትውፊት አጥብቃችሁ ስለ ያዛችሁ፥ አመሰግናችኋለሁ። 3ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴት ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር አብ መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ። 4ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። 5እንዲሁም ራስዋን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የምትናገር ሴት በሴት ላይ ሥልጣን ያለውን ወንድን ታዋርዳለች፤ ራስዋን የማትከናነብ ሴት እንደ ተላጨች ትቈጠራለች። 6ሴት ራስዋን የማትከናነብ ከሆነ ጠጒርዋን ትቈረጥ፤ ነገር ግን ጠጒርዋን መቈረጥ ወይም መላጨት የሚያዋርዳት ነገር ከሆነ ራስዋን ትከናነብ። 7ወንድ የእግዚአብሔር መልክና የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። #ዘፍ. 1፥26-27። 8ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም። 9እንዲሁም ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም፤ #ዘፍ. 2፥18-23። 10በዚህ ምክንያትና በመላእክትም ምክንያት ሴት የሥልጣን ምልክት የሆነውን መከናነቢያ በራስዋ ላይ ታድርግ። 11በጌታ ባለን ሕይወት ሴት ያለ ወንድ አትኖርም፤ ወንድም ያለ ሴት አይኖርም። 12ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች እንዲሁም ወንድ የሚወለደው ከሴት ነው፤ ነገር ግን ወንድም ሆነ ሴት ሌላውም ነገር ሁሉ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነው።
13እስቲ ራሳችሁ ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትከናነብ ወደ እግዚአብሔር መጸለይዋ ተገቢ ነውን? 14ወንድ ጠጒሩን ቢያስረዝም ነውር እንደሚሆንበት ተፈጥሮ ራሱ ያስተምራችሁ የለምን? 15ሴት ግን ጠጒር የተሰጣት ራሷን ልትሸፍንበት ስለ ሆነ ጠጒርዋን ብታስረዝም ለእርስዋ ክብርዋ ነው። 16ስለዚህ ጉዳይ መከራከር የሚፈልግ ሰው ቢኖር እኛም ሆንን ወይም ሌሎች የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያን ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።
የቅዱስ ቊርባን ሥርዓት
(ማቴ. 26፥26-29ማር. 14፥22-25ሉቃ. 22፥14-20)
17በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምታደርጉት ክፉ እንጂ መልካም ነገር ስላልሆነ በዚህ አሁን በምሰጣችሁ ትምህርት አላመሰግናችሁም። 18ከሁሉ በፊት በማኅበር በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት መኖሩን ሰምቼአለሁ፤ የሰማሁትም ነገር በከፊል እውነት መሆኑን አምናለሁ። 19ትክክል የሆኑት እነማን እንደ ሆኑ ተለይተው እንዲታወቁ በመካከላችሁ መለያየት መኖሩ ግድ ነው። 20በአንድነት በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታን ራት አይደለም። 21ስትበሉ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ብቻውን ይበላል፤ በዚህ ሁኔታ አንዱ ሲራብ ሌላው ይሰክራል። 22ኧረ ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትንቃላችሁን? ወይስ ምንም የሌላቸውን ችግረኞች ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? ስለዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ከቶ አላመሰግናችሁም!
23ከጌታ የተቀበልኩትና ለእናንተም ያስተላለፍኩላችሁ ትምህርት ይህ ነው፤ ጌታ አልፎ በተሰጠበት ሌሊት ኅብስት አነሣ፤ 24የምስጋናም ጸሎት አድርጎ ቈረሰውና “[እንካችሁ ብሉ፤] ይህ ለእናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። 25እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው፤ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። #ዘፀ. 24፥6-8፤ ኤር. 31፥31-34።
26ይህን ኅብስት በምትበሉበትና ይህንንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ። 27ማንም ሰው ያልተገባው ሆኖ ሳለ የጌታን ኅብስት ቢበላና የጌታንም ጽዋ ቢጠጣ የጌታን ሥጋና ደም በማቃለሉ ይጠየቅበታል። 28ስለዚህ ማንም ሰው ይህን ኅብስት ከመብላቱና ይህንንም ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት ራሱን መመርመር አለበት። 29ማንም ሰው የጌታ ሥጋ ምን መሆኑን ለይቶ ሳያውቅ የጌታን ኅብስት ቢበላና የጌታን ጽዋ ቢጠጣ በራሱ ላይ ፍርድን ያመጣል። 30ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት አንዳንዶችም የሞቱት በዚሁ ምክንያት ነው። 31በራሳችን ላይ ፈርደን ቢሆን ኖሮ ባልተፈረደብንም ነበር። 32ነገር ግን በኋላ ከዓለም ጋር እንዳንኰነን አሁን ፈርዶ ጌታ ይገሥጸናል።
33ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! ለጌታ ራት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። 34መሰብሰባችሁ ለፍርድ እንዳይሆን ከመካከላችሁ የራበው ሰው ቢኖር በቤቱ ይብላ። ስለ ቀረው ነገር እኔ እዚያ ስመጣ ተጨማሪ መመሪያ እሰጣችኋለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ