የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ቆሮንቶስ 10:1-33

1 ቆሮንቶስ 10:1-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ አባ​ቶ​ቻ​ችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረ​ዳ​ቸው ሁሉም በባ​ሕር መካ​ከል አል​ፈው እንደ ሄዱ ልታ​ውቁ እወ​ዳ​ለሁ። ሁሉ​ንም ሙሴ በደ​መ​ናና በባ​ሕር አጠ​መ​ቃ​ቸው። ሁሉም ያን መን​ፈ​ሳዊ ምግብ ተመ​ገቡ። ሁሉም ያን መን​ፈ​ሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸ​ውም በኋ​ላ​ቸው ከሚ​ሄ​ደው ከመ​ን​ፈ​ሳዊ ዐለት የጠ​ጡት ነው፤ ያም ዐለት ክር​ስ​ቶስ ነበረ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን ከእ​ነ​ርሱ በሁ​ሉም ደስ አላ​ለ​ውም፤ ብዙ​ዎቹ በም​ድረ በዳ ወድ​ቀ​ዋ​ልና። እነ​ርሱ እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ ክፉ እን​ዳ​ን​መኝ እነ​ርሱ ለእኛ ምሳሌ ሆኑ​ልን። “አሕ​ዛብ ተቀ​መጡ፤ ይበ​ሉና ይጠ​ጡም ጀመር፤ ሊዘ​ፍ​ኑም ተነሡ” ብሎ መጽ​ሐፍ እንደ ተና​ገረ ከእ​ነ​ርሱ አን​ዳ​ን​ዶቹ እንደ አመ​ለኩ ጣዖ​ትን የም​ታ​መ​ልኩ አት​ሁኑ። ከእ​ነ​ር​ሱም አን​ዳ​ን​ዶቹ እንደ ሴሰኑ፥ በአ​ንድ ቀንም ሃያ ሦስት ሺህ ሰዎች እንደ ወደቁ አን​ሴ​ስን። ከእ​ነ​ር​ሱም አን​ዳ​ን​ዶቹ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እንደ ተፈ​ታ​ተ​ኑት፥ ነዘር እባ​ብም እንደ አጠ​ፋ​ቸው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አን​ፈ​ታ​ተን። ከእ​ነ​ር​ሱም አን​ዳ​ን​ዶቹ እን​ዳ​ን​ጐ​ራ​ጐ​ሩ​በት፥ በመ​ቅ​ሠ​ፍ​ትም እን​ደ​ጠፉ አና​ን​ጐ​ራ​ጕር። እነ​ር​ሱን ያገ​ኛ​ቸው ይህ ሁሉ ነገር በኋላ ዘመን ለም​ን​ነ​ሣው ለእኛ ትም​ህ​ር​ትና ምክር ሊሆ​ነን ምሳሌ ሆኖ ተጻፈ። አሁ​ንም ያ ቆሜ​አ​ለሁ ብሎ በራሱ የሚ​ታ​መን ሰው እርሱ እን​ዳ​ይ​ወ​ድቅ ይጠ​ን​ቀቅ። በሰው ላይ እን​ደ​ሚ​ደ​ር​ሰው ያለ ፈተና ነው እንጂ ሌላ ፈተና አያ​ገ​ኛ​ች​ሁም። በም​ት​ች​ሉት መከራ ነው እንጂ በማ​ት​ች​ሉት መከራ ትፈ​ተኑ ዘንድ ያል​ተ​ዋ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​መ​ሰ​ገነ ነው፤ እር​ሱም ከፈ​ተና ትድኑ ዘንድ በመ​ከራ ጊዜ ይረ​ዳ​ች​ኋል። ወን​ድ​ሞች! አሁ​ንም ጣዖት ከማ​ም​ለክ ሽሹ። ለዐ​ዋ​ቂ​ዎች እን​ደ​ሚ​ነ​ገር እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ፤ ትክ​ክ​ለ​ኛ​ው​ንም እና​ንተ ራሳ​ችሁ ፍረዱ። ይህ የም​ን​ባ​ር​ከው የበ​ረ​ከት ጽዋ ከክ​ር​ስ​ቶስ ደም ጋር አንድ አይ​ደ​ለ​ምን? የም​ን​ፈ​ት​ተው ይህስ ኅብ​ስት ከክ​ር​ስ​ቶስ ሥጋ ጋር አንድ አይ​ደ​ለ​ምን? ኅብ​ስቱ አንድ እንደ ሆነ እን​ዲሁ እኛም ብዙ​ዎች ስን​ሆን አንድ አካል ነን፤ ሁላ​ችን ከአ​ንድ ኅብ​ስት እን​ቀ​በ​ላ​ለ​ንና። እስ​ራ​ኤል ዘሥ​ጋን ተመ​ል​ከቱ፤ መሥ​ዋ​ዕ​ቱን ይበ​ላሉ፤ ከመ​ሠ​ዊ​ያ​ውም ጋር አንድ ይሆኑ አል​ነ​በ​ረ​ምን? እን​ግ​ዲህ ምን እን​ላ​ለን? ለጣ​ዖ​ታት የሚ​ሠዋ መሥ​ዋ​ዕት ከንቱ ነው፤ ጣዖ​ቶ​ቻ​ቸ​ውም ከንቱ ናቸው። አሕ​ዛ​ብም የሚ​ሠዉ ለአ​ጋ​ን​ንት ነው እንጂ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አይ​ደ​ለም፤ ነገር ግን የአ​ጋ​ን​ንት ተባ​ባ​ሪ​ዎች እን​ድ​ት​ሆኑ አል​ፈ​ቅ​ድ​ላ​ች​ሁም። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ጽዋና የአ​ጋ​ን​ን​ትን ጽዋ አንድ አድ​ር​ጋ​ችሁ መጠ​ጣት አት​ች​ሉም፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ማዕ​ድና የአ​ጋ​ን​ን​ት​ንም ማዕድ በአ​ን​ድ​ነት ልት​በሉ አት​ች​ሉም። እን​ግ​ዲህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እና​ስ​ቀ​ና​ውን? በውኑ እኛ ከእ​ርሱ እን​በ​ረ​ታ​ለን? ሁሉ ተፈ​ቅ​ዶ​ል​ኛል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚ​ጠ​ቅም አይ​ደ​ለም፤ ሁሉ ተፈ​ቅ​ዶ​ል​ኛል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚ​ያ​ንጽ አይ​ደ​ለም። ለባ​ል​ን​ጀ​ራ​ችሁ እንጂ ለራ​ሳ​ችሁ አታ​ድሉ። ደግ​ሞም በሥጋ ገበያ የሚ​ሸ​ጡ​ትን ሁሉ ከሕ​ሊና የተ​ነሣ ሳት​መ​ራ​መሩ ብሉ። “ምድር በመ​ላዋ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ናትና።” ያላ​መነ ሰው ቢጠ​ራ​ችሁ፥ ልት​ሄ​ዱም ብት​ወዱ ያቀ​ረ​ቡ​ላ​ች​ሁን ሁሉ ከሕ​ሊና የተ​ነሣ ሳት​መ​ራ​መሩ ብሉ። እን​ግ​ዲህ “ይህ ለጣ​ዖት የተ​ሠዋ ነው” ያላ​ችሁ ቢኖር ግን፥ ስለ ነገ​ራ​ች​ሁና ባል​ን​ጀ​ራ​ች​ሁም የሚ​ጠ​ራ​ጠር ስለ​ሆነ አት​ብሉ። ነጻ​ነ​ታ​ች​ሁን እን​ዳ​ይ​ነ​ቅ​ፉ​አት አስ​ረ​ድ​ተ​ዋ​ች​ኋ​ልና። በጸጋ ብበላ ግን በነ​ገሩ ስለ​ማ​መ​ሰ​ግን ለምን ይነ​ቅ​ፉ​ኛል። ብት​በ​ሉም፥ ብት​ጠ​ጡም የም​ታ​ደ​ር​ጉ​ትን ሁሉ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ክብር አድ​ር​ጉት። ለአ​ይ​ሁ​ድም፥ ለአ​ረ​ማ​ው​ያ​ንም፥ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤተ ክር​ስ​ቲ​ያ​ንም ያለ ማሰ​ና​ከል አር​አያ ሁኑ​አ​ቸው። እኔም ሁሉን በሁሉ ነገር ደስ እን​ዳ​ሰኝ ይድኑ ዘንድ የብ​ዙ​ዎ​ችን ተድላ እሻ​ለሁ እንጂ የራ​ሴን ተድላ የምሻ አይ​ደ​ለ​ሁ​ምና።

1 ቆሮንቶስ 10:1-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወንድሞች ሆይ፤ አባቶቻችን ሁሉ ከደመናው በታች እንደ ነበሩና በባሕሩ ውስጥ እንደ ተሻገሩ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ። እነርሱ ሁሉ ከሙሴ ጋር ለመተባበር በደመናና በባሕር ተጠመቁ። ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤ ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዐለት ጠጥተዋልና፤ ያ ዐለት ክርስቶስ ነበረ። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በብዙዎቹ ደስ ስላልተሰኘ በበረሓ ወድቀው ቀሩ። እነርሱ ክፉ እንደ ተመኙ፣ እኛም ደግሞ እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ሆነውልናል። “ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው በአንድ ቀን ሃያ ሦስት ሺሕ ሰው እንደ ረገፈ፣ እኛም ዝሙት አንፈጽም። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑና በእባብ ተነድፈው እንደ ጠፉ፣ እኛም ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጕረመረሙና በአጥፊው እንደ ጠፉ፣ አታጕረምርሙ። ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ። ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። ይህን የምናገረው አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ ስለምናገረው ነገር እናንተው ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። እስቲ የእስራኤልን ሕዝብ አስቡ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን? ታዲያ፣ ለጣዖት የተሠዋ ነገርም ሆነ ጣዖቱ ራሱ ዋጋ ያለው ነገር ነው ማለቴ ነውን? አይደለም፤ አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ከአጋንንት ጋር እንድትተባበሩም አልሻም። የጌታን ጽዋና፣ የአጋንንትን ጽዋ በአንድ ላይ መጠጣት አትችሉም፤ ከጌታ ማእድና ከአጋንንት ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም። ጌታን እናስቀናውን? በብርታትስ ከእርሱ እንበልጣለንን? “ሁሉ ነገር ተፈቅዷል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉም ነገር ተፈቅዷል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አያንጽም። እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ። በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ፣ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ ምድርና በውስጧ ያለው ሁሉ የጌታ ነውና። የማያምን ሰው ጋብዟችሁ ለመሄድ ብትፈልጉ በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ የቀረበላችሁን ሁሉ ብሉ። ነገር ግን አንዱ፣ “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ፣ ይህን ስለ ነገራችሁ ሰውና ለኅሊናችሁ ስትሉ አትብሉ። ይህን የምለውም ስለዚያ ሰው ኅሊና እንጂ ስለ አንተ አይደለም፤ ነጻነቴስ በሌላ ሰው ኅሊና ለምን ይመዘን? ምግቡን በምስጋና የምበላ ከሆነ፣ እግዚአብሔርን ባመሰገንሁበት ነገር ለምን እወቀሣለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። ለአይሁድም ሆነ ለግሪኮች ወይም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መሰናክል አትሁኑ፤ እኔ ሰውን ሁሉ በማንኛውም ረገድ ለማስደሰት እንደምጥር እናንተም እንዲሁ አድርጉ፤ ብዙዎችም ይድኑ ዘንድ፣ ለራሴ የሚጠቅመውን ሳይሆን ለእነርሱ የሚጠቅመውን እሻለሁና።

1 ቆሮንቶስ 10:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ። እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና። እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን። ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጕኦርጕሩ። ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው እላለሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ። በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤ ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነውና። ከማያምኑ ሰዎች አንዱም ቢጠራችሁ ልትሄዱም ብትወዱ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ። ማንም ግን፦ ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው ቢላችሁ ከዚያ ካስታወቃችሁና ከሕሊና የተነሣ አትብሉ፤ ስለ ባልንጀራህ ሕሊና እንጂ ስለ ገዛ ሕሊናህ አልናገርም። አርነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ ኧረ ስለ ምንድር ነው? እኔም በጸጋ ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለ ምን እሰደባለሁ? እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ፥ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ።

1 ቆሮንቶስ 10:1-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞቼ ሆይ! አባቶቻችን ደመና ከበላያቸው ሆኖ ይመራቸው እንደ ነበረና ሁሉም ቀይ ባሕርን እንደ ተሻገሩ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። የሙሴ ተባባሪዎች ለመሆንም በዚህ ደመናና በዚህ ባሕር ተጠመቁ። ሁሉም አንድ ዐይነት መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ። ሁሉም አንድ ዐይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ የጠጡትም ይከተላቸው ከነበረው ከዚያ ከመንፈሳዊ አለት የመነጨ ነበር፤ ያም አለት ራሱ ክርስቶስ ነበር። ይህም ሆኖ እግዚአብሔር በአብዛኞቹ አልተደሰተም፤ ስለዚህ ሬሳቸው በበረሓ ወድቆ ቀረ። እነርሱ ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛም ክፉ ነገር እንዳንመኝ ይህ ሁሉ ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሆኖናል። “ሰዎች ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ከመጠን በላይ ሊፈነጥዙ ተነሡ” ተብሎ ስለ እነርሱ እንደ ተጻፈው፥ እነርሱ ጣዖትን እንዳመለኩ እናንተም እንደእነርሱ ጣዖትን አታምልኩ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ የዝሙት ኃጢአት እንደ ሠሩ እኛም የዝሙት ኃጢአት እንሥራ፤ እነርሱ ይህን በማድረጋቸው ከእነርሱ ኻያ ሦስት ሺህ ሰዎች በአንድ ቀን ሞተዋል። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑትና በእባብ ተነድፈው እንደ ሞቱ እኛም ጌታን አንፈታተነው። ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጒረመረሙና በቀሳፊው መልአክ እንደ ጠፉ እናንተም አታጒረምርሙ። ይህ ሁሉ ነገር የደረሰባቸው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እንዲሆን ነው፤ የተጻፈውም በዘመናት መጨረሻ ላይ ለምንገኘው ለእኛ ትምህርት እንዲሆነን ነው። ስለዚህ የቆመ የሚመስለው ሰው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። በሰው ከሚደርሰው ፈተና በቀር ሌላ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ከአቅማችሁ በላይ የሆነ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ በምትፈተኑበትም ጊዜ የምትታገሡበትን ኀይል በመስጠት ከፈተናው የምትወጡበትን መንገድ ያዘጋጅላችኋል። እንግዲህ ወዳጆቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ራቁ። ይህንንም የምላችሁ አስተዋዮች በመሆናችሁ ነው፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛ እግዚአብሔርን አመስግነን የምንካፈለው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰው ኅብስት ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? ኅብስቱ አንድ በመሆኑ እኛም ከዚህ ከአንዱ ኅብስት የምንካፈል ስለ ሆንን ምንም እንኳ ብዙዎች ብንሆን አንድ አካል ነን። እስቲ የእስራኤል ሕዝብ ያደረጉትን ተመልከቱ፤ የሚቀርበውን መሥዋዕት የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን? ታዲያ ይህን ስል ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ የሚረባ ነገር ነው ማለቴ ነውን? ወይስ ጣዖት የሚረባ ነገር ነው ማለቴ ነውን? አይደለም! አሕዛብ መሥዋዕት የሚያቀርቡት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ስለዚህ እናንተ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አልፈልግም፤ የጌታን ጽዋ እየጠጣችሁ ደግሞ የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም፤ የጌታ ማእድ ተካፋዮች ሆናችሁ ደግሞ የአጋንንትን ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም፤ ታዲያ ይህን በማድረግ ጌታን እናስቀናውን? እኛ ከእርሱ ይበልጥ እንበረታለንን? ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ ነገር ጠቃሚ አይደለም፤ ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ ነገር የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም ብቻ አይፈልግ። ከኅሊናችሁ የሚነሣውን ጥርጣሬ አስወግዳችሁ ማንኛውንም በገበያ የሚሸጠውን ሥጋ ሳታመነቱ ብሉ። “ምድርና በእርስዋም ያለው ሁሉ የጌታ ነው።” ክርስቲያን ያልሆነ ሰው ቢጋብዛችሁና ግብዣውንም ብትቀበሉ የሚቀርብላችሁን ማንኛውንም ምግብ ከኅሊናችሁ የሚነሣውን ጥርጣሬ አስወግዳችሁ ሳታመነቱ ብሉ። ነገር ግን አንድ ሰው “ይህ ሥጋ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ ይህን በነገራችሁ ሰው ምክንያትና በኅሊናም ምክንያት ሥጋውን አትብሉ። ኅሊናም ስላችሁ የሰውዬውን ኅሊና ማለቴ ነው እንጂ የእናንተን ኅሊና ማለቴ አይደለም፤ ታዲያ በሌላው ሰው ኅሊና ምክንያት በእኔ ነጻነት ላይ የሚፈረደው ለምንድን ነው? እኔ እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ብበላ እግዚአብሔርን በማመሰግንበት ነገር ስለምን እወቀስበታለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማናቸውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉ። አይሁድንም ቢሆን፥ አሕዛብንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን ቢሆን፥ ማንንም አታሰናክሉ። እኔ ሁሉም እንዲድኑ የሌሎችን ጥቅም እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ ሰውን ሁሉ በማደርገው ነገር ሁሉ እንደማስደስት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።

1 ቆሮንቶስ 10:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞች ሆይ! ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ፤ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን እንዲተባበሩ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤ ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ የጠጡትም ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዐለት ነበር፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ። እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በአብዛኞቹ ደስ አልተሰኘም፤ እነርሱ ምድረ በዳ ወድቀው ቀርተዋልና። እነርሱ ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛም እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ሆኑልን። “ሕዝቡም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ አንሴስን፥ በአንዲት ቀን ሃያ ሦስት ሺህ ወድቀዋልና። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑትና በእባቦች እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳጉረመረሙና በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታጉረምርሙ። ይህ ሁሉ ነገር እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፤ የተጻፈው ግን በዘመናት መጨረሻ ለምንገኘው ለእኛ ተግሣጽ ነው። ስለዚህ የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። በሰው ከሚደርሰው ፈተና በቀር ምንም አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፤ መታገሥ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫ መንገድ ደግሞ ያዘጋጅላችኋል። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ የምለውን ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ፥ የክርስቶስን ደም መካፈል አይደለምን? የምንቆርሰውስ ኀብስት፥ የክርስቶስን ሥጋ መካፈል አይደለምን? አንድ ኀብስት ስለ ሆነ፥ ሁላችን ያን አንዱን ኀብስት እንካፈላለንና፥ እኛ ብዙዎች ብንሆንም አንድ አካል ነን። በሥጋ የሆነውን እስራኤልን ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ የሚረባ ነገር ነው? ወይስ ጣዖት የሚረባ ነገር ነው? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት፤ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አልፈልግም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም አይፈልግ። ከሕሊና የተነሣ ሳትጠራጠሩ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ ምድር የጌታ ነውና፥ በእርሷ የሞላባት ሁሉ። ከማያምኑ ሰዎች አንዱ ቢጠራችሁ እናንተም ለመሄድ ብትፈልጉ ከሕሊና የተነሣ ሳትጠራጠሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ። ማንም ግን “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው፤” ቢላችሁ ይህን በነገራችሁ ሰው ምክንያትና በኅሊናም ምክንያት ሥጋውን አትብሉ፤ ስለ ሌላው ሰው ሕሊና ማለቴ እንጂ ስለ ራሳችሁ ሕሊና አይደለም። ነጻነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ ኧረ ለምንድን ነው? እኔም በምስጋና ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለምን እሰደባለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማናቸውንም ነገር ስታደርጉ፥ ሁሉን ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። ለአይሁድም ይሁን ለግሪክም እንዲሁም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ማሰናከያ አትሁኑ። እኔ ደግሞ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ ነገር ግን ብዙዎቹ እንዲጠቀሙ፥ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ ለማሰኘት የምጥረው፥ ይድኑ ዘንድ ነው።