1 ዜና መዋዕል 16:23-28
1 ዜና መዋዕል 16:23-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ማዳኑንም ዕለት ዕለት ዐውጁ። ክብሩን ለአሕዛብ ተናገሩ፤ ድንቅ ሥራዎቹን ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ምስጋናውም ብዙ ነው፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ የሚገባው ነው። የአሕዛብ ሁሉ አማልክት ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። በፊቱ ክብርና ሞገስ አለ፤ ብርታትና ደስታም በማደሪያው ስፍራ። የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ክብርና ኀይልን ለእግዚአብሔር አምጡ።
1 ዜና መዋዕል 16:23-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ዕለት ዕለት ማዳኑን አውሩ። ክብሩን ለአሕዛብ፥ ተአምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ። እግዚአብሔር ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፤ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኀይልና ደስታ በስፍራው ውስጥ ናቸው። የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ክብርንና ኀይልን ለእግዚአብሔር አምጡ።
1 ዜና መዋዕል 16:23-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ። ክብሩን ለአሕዛብ፥ ተአምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ። እግዚአብሔር ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፤ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኀይልና ደስታም በመቅደሱ ውስጥ ናቸው። እናንተ የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር አምጡ፥ ክብርንና ኀይልን ለእግዚአብሔር አምጡ።
1 ዜና መዋዕል 16:23-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ! የአዳኝነቱን መልካም ዜና በየቀኑ አብሥሩ፤ በሕዝቦች መካከል ክብሩን አስታውቁ፤ ለሕዝቦችም ሁሉ ታላቅ ሥራውን አውሩ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ከፍ ያለ ምስጋናም ይገባዋል፤ ከአማልክት ሁሉ ይበልጥ ሊፈራ ይገባዋል፤ ሌሎች ሕዝቦች የሚሰግዱላቸው አማልክት ጣዖቶች ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን የፈጠረ አምላክ ነው። በዙሪያው ያለው ክብርና ግርማ ነው፤ መቅደሱንም ኀይልና ደስታ እንዲሞላበት አድርጎአል። በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ! ስለ ክብሩና ስለ ኀይሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት።
1 ዜና መዋዕል 16:23-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ምድር ሁሉ ጌታን አመስግኑ፤ ዕለት ዕለት ማዳኑን አውሩ። ክብሩን ለአሕዛብ፥ ተአምራቱንም ለሰዎች ሁሉ ንገሩ። ጌታ ታላቅ፥ ከፍ ያለ ምስጋናም ይገባዋልና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ የተፈራ ነው። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ ጌታ ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኃይልና ደስታ በስፍራው ውስጥ ናቸው። የአሕዛብ ወገኖች ለጌታ የሚገባውን ስጡ፥ ለጌታ ተገቢውን ክብርና ኃይል ስጡ።