መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 16
16
1የእግዚአብሔርንም ታቦት ይዘው ገቡ፤ ዳዊትም በተከለላት ድንኳን ውስጥ አኖሩአት፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕትም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። 2ዳዊትም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ማቅረብ በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ሕዝቡን ባረከ። 3ለእስራኤልም ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም ቍራጭ ሥጋ፥#“አንዳንድም ቍራጭ ሥጋ” የሚለው በግሪኩ የለም። አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አካፈለ።
4በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት ያገለግሉ ዘንድ፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ያወድሱት ዘንድ፥ ያመሰግኑትና ያከብሩትም ዘንድ ከሌዋውያን ወገን አቆመ። 5አለቃውም አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱም ቀጥሎ ዘካርያስ፥ ኢያሔል፥ ሰሜራሞት፥ ይሔኤል፥ ማታትያ፥ ኤልያብ፥ በናያስ፥ አብዲዶም፥ ይዒኤል በመሰንቆና በበገና፥ አሳፍም በጸናጽል ይዘምሩ ነበር። 6ካህናቱም በናያስና የሕዜኤል በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ሁልጊዜ መለከት ይነፉ ነበር።
7በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ እጅ እግዝአብሔርን እንዲያመሰግኑ አስቀድሞ ትእዛዝን ሰጠ።
የምስጋና መዝሙር
(መዝ. 104፥1-15፤ 95፥1-3፤ 105፥47-48)
8የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት የዘመርዋት መዝሙር ይህች ናት፦
እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ስሙንም ጥሩ፤
ለአሕዛብም ሥራውን አውሩ።
9ለእግዚአብሔር ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፤
እግዚአብሔርም ያደረገውን ተአምራቱን ሁሉ ተናገሩ።
10በቅዱስ ስሙ ክበሩ፤
እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።
11እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤
ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።
12የሠራትን ድንቅ አስቡ፥
ተአምራቱንም፥ የአፉንም ፍርድ፤
13ባሪያዎቹ የእስራኤል#ግእዙ “የአብርሃም” ይላል። ዘር፥
ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥
14እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤
ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው።
15ቃል ኪዳኑን ለዘለዓለም፥
እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አስቡ” ይላል።
16ለአብርሃም ያደረገውን፥
ለይስሐቅም የማለውን፤
17ለያዕቆብ ሥርዐት እንዲሆን
ለእስራኤልም የዘለዓለም ኪዳን እንዲሆን አጸና፤
18እንዲህም አለ፥ “ለአንተ የከነዓንን ምድር
የርስታችሁን ገመድ እሰጣለሁ፤”
19ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች፥
እጅግ ጥቂቶችና ስደተኞች ሲሆኑ ነው።
20ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥
ከመንግሥትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ።
21ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፤
ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።
22“የቀባኋቸውን አትንኩ፥
በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ” ብሎ፥
23ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ።
24ክብሩን ለአሕዛብ፥
ተአምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ።
25እግዚአብሔር ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፤
በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው።
26የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
27ክብርና ግርማ በፊቱ፥
ኀይልና ደስታም በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።
28እናንተ የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር አምጡ፥
ክብርንና ኀይልን ለእግዚአብሔር አምጡ።
29ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤
ቍርባንን ይዛችሁ በአደባባዩ ግቡ፤
በቅድስናውም ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።
30ምድር ሁሉ በፊቱ ትነዋወጣለች፤
ዓለምንም እንዳትነዋወጥ አጸናት።#ዕብ. “ዓለሙም እንዳይናወጥ ጸንቶአል” ይላል።
31ሰማያት ደስ ይበላቸው፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ፤
በአሕዛብ መካከል፥ “እግዚአብሔር ነገሠ” በሉ።
32ባሕር በሞላዋ ትናወጣለች፤
በረሃ በእርስዋም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ።
33በምድር ሊፈርድ ይመጣልና፥
የዱር ዛፎች በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል።
34እግዚአብሔርን አመስግኑ።
ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና።
35የመዳናችን አምላክ ሆይ፥ አድነን፤
ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥
በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥
ከአሕዛብ ሰብስበህ ታደገን በሉ።
36ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም፥
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። ሕዝቡ ሁሉ አሜን ይበሉ፤
እግዚአብሔርንም ያመስግኑ።
ሥርዐተ አምልኮ
37እንዲሁም በየቀኑ እንደሚገባቸው በታቦቱ ፊት ዘወትር ያገለግሉ ዘንድ አሳፍንና ወንድሞቹን ተዋቸው። 38አብዲዶምንም፥ ስድሳ ስምንቱንም ወንድሞቻቸውን፤ የኤዶታምም ልጅ አብዲዶምና ሖሳ በረኞች ይሆኑ ዘንድ ተዋቸው፤ 39ካህኑን ሳዶቅንና ካህናቱን ወንድሞቹን በገባዖን በኮረብታው መስገጃ ባለው በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት አቆማቸው፥ 40ለእስራኤልም ልጆች ይነግራቸው ዘንድ አገልጋዩ ሙሴን እንደ አዘዘው በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈ ሁሉ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁልጊዜ ጥዋትና ማታ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ። 41ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ኤማንንና ኤዶታምን፥ በስማቸው የተጻፉትን ተመርጠው የቀሩትን ከእነርሱ ጋር አቆመ። 42ከእነርሱም ጋር ካህናቱ ከፍ አድርገው ለማሰማት መለከትና ጸናጽል ለእግዚአብሔርም መዝሙራት የዜማ ዕቃ ይዘው ነበር፤ የኤዶታም ልጆች ግን በረኞች ነበሩ። 43ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ዳዊትም ቤቱን ይባርክ ዘንድ ተመለሰ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 16: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ