የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ሩት 2:1-13

መጽሐፈ ሩት 2:1-13 አማ54

ለኑኃሚንም ባል የሚዘመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ። ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን “በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ፤” አለቻት። እርስዋም “ልጄ ሆይ! ሂጂ፤” አለቻት። ሄደችም፤ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፤ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፤ አጫጆችንም “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር ይባርክህ፤” ብለው መለሱለት። ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን “ይህች ወጣት ሴት የማን ናት?” አለው። የአጫጆቹም አዛዥ “ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፤ እርስዋም ‘ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም እባክህ ፍቀድልኝ’ አለች፤ መጣችም፤ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም፤” አለው። ቦዔዝም ሩትን “ልጄ ሆይ! ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፤ ከዚህም አትላወሺ፤ ነገር ግን ገረዶቼን ተጠጊ። ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፤ ተከተያቸውም፤ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፤ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውሃ ጠጪ፤” አላት። በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት “እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን?” አለችው። ቦዔዝም “ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ። እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን፤” አላት። እርስዋም “ጌታዬ ሆይ! ከባሪያዎችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባሪያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዐይንህ ሞገስ ላግኝ፤” አለችው።