መጽሐፈ ሩት 2:1-13

መጽሐፈ ሩት 2:1-13 አማ05

ለናዖሚም ሀብታምና ታዋቂ የሆነ ቦዔዝ የሚባል የባልዋ የአቤሜሌክ የቅርብ ዘመድ ነበራት፤ አንድ ቀን ሞአባዊትዋ ሩት ናዖሚን “በፊቱ ሞገስ ወደማገኝበት ሰው እርሻ ሄጄ ቃርሚያ ልቃርም” አለቻት። ናዖሚም “ልጄ ሆይ! ሂጂ!” አለቻት። ሩትም ወደ እርሻዎች ሄደች፤ ከአጫጆች ኋላ እየተከተለችም ከእጃቸው የወዳደቀውን ዛላ ትቃርም ጀመር፤ እንደ አጋጣሚ የምትቃርምበት ቦታ የአቤሜሌክ ዘመድ የሆነው የቦዔዝ እርሻ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቦዔዝ ራሱ ከቤተልሔም ተነሥቶ ወደ እርሻው መጣ፤ አጫጆቹንም “እንደምን ዋላችሁ! እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር አንተንም ይባርክህ!” አሉት። ከዚህ በኋላ ቦዔዝ የአጫጆቹ ኀላፊ የሆነውን ሰው “ያቺ ወጣት ሴት ማን ናት?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እርስዋ ናዖሚን ተከትላ ከሞአብ አገር የመጣች ሞአባዊት ናት፤ አጫጆችን ተከትላ ከነዶ መካከል የወዳደቀውን ዛላ ለመቃረም እንድፈቅድላት ጠየቀችኝ፤ ከጧት ጀምራ እስከ አሁን ስትቃርም ነበር፤ አሁን ግን ትንሽ ዕረፍት ለማድረግ ወደ ዳስ ተጠግታለች።” በዚህ ጊዜ ቦዔዝ ሩትን እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ! ስሚ እዚህ ያሉትን ሴቶች ሠራተኞችን ተከትለሽ ቃርሚ እንጂ ይህን እርሻ ትተሽ ለመቃረም ወደ ሌላ ቦታ አትሂጂ። እነርሱ የት እንደሚያጭዱ በመጠባበቅ እየተመለከትሽ ከእነርሱ ጋር ሁኚ፤ ወንዶች ሠራተኞቼን እንዳያስቸግሩሽ አስጠንቅቄአቸዋለሁ፤ ውሃም በሚጠማሽ ጊዜ እነርሱ ሞልተው ወዳስቀመጡአቸው እንስራዎች እየሄድሽ ቀድተሽ ጠጪ።” እርስዋም ግንባርዋ መሬት እስኪነካ ድረስ እጅ ነሥታ “እኔ ባዕድ ሆኜ ሳለ ስለ እኔ ታስብ ዘንድ እንዴት በፊትህ ሞገስ ላገኝ ቻልኩ?” አለችው። ቦዔዝም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ባልሽ ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ ለዐማትሽ ያደረግሽላትን መልካም ነገር ሁሉ፥ እንዲሁም አባትሽንና እናትሽን፥ የትውልድ አገርሽንም ትተሽ ከዚህ በፊት በማታውቂው ሕዝብ መካከል ለመኖር ወደዚህ እንደ መጣሽ ሰምቼአለሁ። እግዚአብሔር ላደረግሽው በጎ ነገር ዋጋሽን ይክፈልሽ! የእርሱን ጥበቃ ተማምነሽ የመጣሽው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ዋጋሽን የተትረፈረፈ ያድርገው!” ሩትም “ጌታዬ ሆይ! ምንም እንኳ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዲቱ ባልሆን እኔን አገልጋይህን በመልካም ቃላት አጽናንተኸኛል፤ ይህ በፊትህ ያገኘሁት ሞገስ እንዲቀጥል ፍቀድልኝ!” አለችው።