ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:1-18

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:1-18 አማ54

በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቍኦጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ።