ከክርስቶስ ጋራ ካላችሁ አንድነት የተነሣ የትኛውም መበረታታት፣ ከፍቅር የሆነ መጽናናት፣ የመንፈስ ኅብረት፣ ምሕረትና ርኅራኄ ካላችሁ፣ በአንድ ሐሳብ፣ በአንድ ፍቅር፣ በአንድ መንፈስና በአንድ ዐላማ በመሆን ደስታዬን ፍጹም አድርጉልኝ። ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው። የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቍርባን ብፈስስ እንኳ ከሁላችሁ ጋራ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ። እናንተም እንደዚሁ ከእኔ ጋራ ደስ ልትሠኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል።
ፊልጵስዩስ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ፊልጵስዩስ 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ፊልጵስዩስ 2:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች