ከዚያም በኋላ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ፤ ታነጻቸውማለህ፥ ስጦታም አድርገህ ታቀርባቸዋለህ። እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና፤ በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ማኅፀን በሚከፍት ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ። በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው። በእስራኤልም ልጆች በኵራት ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ። የእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደሱ በቀረቡ ጊዜ መቅሠፍት እንዳያገኛቸው፥ ለእስራኤል ልጆች ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአቸዋለሁ። ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው። ሌዋውያንም ከኃጢአት ተጣጠቡ፥ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ስጦታ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፥ አሮንም ያነጻቸው ዘንድ አስተሰረየላቸው። ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ይሠሩ ዘንድ ገቡ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የሌዋውያን ሕግ ይህ ነው፤ ከሀያ አምስት ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት በመገናኛው ድንኳን ሥራ ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ። ዕድሜአቸውም አምሳ ዓመት ሲሞላ የአገልግሎታቸውን ሥራ ይተዋሉ፥ ከዚያም በኋላ አይሠሩም፤ የተሰጣቸውን ይጠብቁ ዘንድ ወንድሞቻቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለግላሉ፤ የድንኳኑን አገልግሎት አይሠሩም። እንዲሁ ስለ ሥራቸው በሌዋውያን ላይ ታደርጋለህ።
ኦሪት ዘኊልቊ 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኊልቊ 8:15-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች