ኦሪት ዘኊልቊ 4
4
1እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2ከሌዊ ልጆች መካከል በየወገናቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች የቀዓትን ልጆች ድምር ውሰድ፤ 3ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በመገናኛው ድንኳን ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡበትን ሁሉ ትደምራለህ። 4በመገናኛው ድንኳን በንዋየ ቅድሳቱ ዘንድ የቀዓት ልጆች ሥራ ይህ ነው፤ 5ከሰፈሩ በተነሡ ጊዜ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚሸፍነውን መጋረጃ ያውርዱ፥ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤ 6በላዩም የአስቆጣውን ቁርበት መሸፈኛ ያድርጉበት፥ ከእርሱም በላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። 7በገጽ ኅብስት ገበታ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ ወጭቶቹን፥ ጭልፋዎቹንም፥ ጽዋዎቹንም፥ ለማፍሰስም መቅጃዎቹን ያድርጉ፤ ሁልጊዜም የሚኖር እንጀራ በእርሱ ላይ ይሁን። 8በእነርሱም ላይ ቀይ መጐናጸፊያ ይዘርጉ፥ በአቆስጣውም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። 9ሰማያዊውንም መጐናጸፊያ ይውሰዱ፥ የሚያበራውንም መቅረዝ፥ ቀንዲሎቹንም፥ መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም፥ እርሱንም ለማገልገል የዘይቱን ዕቃዎች ሁሉ ይሸፍኑ፤ 10እርሱንና ዕቃዎቹን ሁሉ በአቆስጣ ቁርበት መሸፈኛ ውስጥ ያድርጉ፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት። 11በወርቁም መሠዊያ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። 12በመቅደስም ውስጥ የሚያገልግሉበትን የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ ይውሰዱ፥ በሰማያዊውም መጐናጸፊያ ውስጥ ያስቀምጡት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት። 13አመዱንም ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፥ ሐምራዊውንም መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ 14የሚያገለግሉበትን ዕቃውን ሁሉ፥ ማንደጃዎቹን ሜንጦቹንም መጫሪያዎቹንም ድስቶቹንም፥ የመሠዊያውን ዕቃ ሁሉ ያስቀምጡበት፤ በእርሱም የአቆስጣን ቁርበት መሸፈኛ ይዘርጉ፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። 15ከሰፈሩም ሲነሡ፥ አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃ ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ። በመገናኛው ድንኳን ዘንድ የቀዓት ልጆች ሸክም ይህ ነው። 16የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት በጣፋጩም ዕጣን ላይ፥ ሁልጊዜም በሚቀርበው በእህሉ ቍርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ይሾም፤ ማደሪያውን ሁሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ መቅደሱንና ዕቃውን ይጠብቃል። 17እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 18የቀዓትን ወገኖች ነገድ ከሌዋውያን መካከል አታጥፉአቸው፤ 19ነገር ግን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በቀረቡ ጊዜ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እንጂ እንዳይሞቱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ይግቡ፥ ለሰውም ሁሉ ሥራውንና ሸክሙን ይዘዙ፤ 20ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋየ ቅድሳቱን ለድንገት እንኳ ለማየት አይግቡ። 21እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 22የጌድሶንን ልጆች ድምር ደግሞ በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገኖቻቸውም ውሰድ። 23የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው። 24የጌድሶናውያን ወገኖች ሥራ በማገልገልና በመሸከም ይህ ነው፤ 25የማደሪያውን መጋረጆች፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መደረቢያውን፥ በላዩም ያለውን የአቆስጣውን ቁርበት መደረቢያ፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ 26በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለውን የአደባባዩን መጋረጃ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቻቸውንም፥ ለማገልገልም የሚሠሩበትን ዕቃ ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህ ያገልግሉ። 27የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፥ ሸክማቸውም ሁሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ ትእዛዝ ይሁን፤ የሚደርስባቸውንም ሸክም ሁሉ ትነግሩአቸዋላችሁ። 28የጌድሶናውያን ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ይህ ነው፤ ከካህኑ ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ይሆናሉ። 29የሜራሪንም ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቍጠራቸው። 30የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው። 31በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ፥ የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎቹም፥ ተራዳዎቹም፥ እግሮቹም፥ 32በዙሪያውም የሚቆሙት የአደባባዩ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም፥ ዕቃዎቹና ማገልገያዎቹ ሸክማቸው ነው፤ የሚጠብቁትንም የሸክማቸውን ዕቃ ሁሉ በስማቸው ቍጠሩ። 33የሜራሪ ልጆች ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ከካህኑ ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች በየአገልግሎታቸው ሁሉ ይህ ነው። 34ሙሴና አሮንም የሕቡም አለቆች የቀዓትን ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቈጠሩአቸው። 35በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ወደ አገልግሎት የገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቈጠሩአቸው፤ 36በየወገናቸውም ከእነርሱ የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ። 37እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከቀዓታውያን ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። 38በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት የጌድሶን ልጆች፥ 39በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የገቡት፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ 40በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 41እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከጌድሶን ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። 42በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ 43በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወደ አገልግሎት የገቡት ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ 44በየወገናቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 45እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። 46በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሌዋውያን የተቈጠሩት ሁሉ፥ ሙሴና አሮን የእስራኤልም አለቆች የቈጠሩአቸው፥ 47በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራትና ዕቃውን ለመሸከም የገቡት ሁሉ፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ 48ከእነርሱ የተቈጠሩት ስምንት ሺህ ኣምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ። 49እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ እያንዳንዳቸው በየአገልግሎታቸውና በየሸክማቸው በሙሴ እጅ ተቈጠሩ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በእርሱ ተቈጠሩ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 4: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ