ኦሪት ዘኊልቊ 5
5
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ፥ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፥ በሬሳም የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤ 3ወንዱንና ሴቱን አውጡ፤ እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈሩ አወጡአቸው። 4የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ። 5እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 6ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፦ ወንድ ወይም ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፍ ዘንድ ሰው የሚሠራውን ኃጢአት ቢሠራ፥ በዚያም ሰው ላይ በደል ቢሆን፥ በሠራው ኃጢአት ይናዘዝ፤ 7የወሰደውንም በሙሉ ይመልስ አምስተኛውንም ይጨምርበት፥ ለበደለውም ሰው ይስጠው። 8ነገር ግን ይመልስለት ዘንድ ሰውዮው ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለእግዚአብሔር የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሁን፥ ይህም ስለ እርሱ ማስተስረያ ከሚደረግበት አውራ በግ በላይ ይጨመር። 9የእስራኤልም ልጆች ለካህኑ የሚያቀርቡት የተቀደሰ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለእርሱ ይሁን። 10የተቀደሰ የሰው ነገር ሁሉ፥ ሰውም ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ለእርሱ ይሁን። 11እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 12ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፦ የማንኛውም ሰው ሚስት ከእርሱ ፈቀቅ ብትል፥ በእርሱም ላይ ብትበድል፥ 13ከሌላም ሰው ጋር ብትተኛ፥ ከባልዋም ዓይን ቢሸሸግ፥ እርስዋም ተሰውራ ብትረክስ፥ ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትገኝ፥ 14በባልዋም ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርስዋም ስትረክስ ስለ ሚስቱ ቢቀና፤ ወይም እርስዋ ሳትረክስ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤ ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ 15የኢፍ መስፈሪያም አሥረኛ እጅ ገብስ ዱቄት ቍርባን ስለ እርስዋ ያምጣ፤ የቅንዓት ቍርባን ነውና፥ ኃጢአትንም የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፥ ዕጣንም አይጨምርበት። 16ካህኑም ያቀርባታል በእግዚአብሔርም ፊት ያቆማታል፤ 17ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ካህኑም በማደሪያው ውስጥ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃ ላይ ይረጨዋል፤ 18ካህኑም ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፥ የሴቲቱንም ራስ ይገልጣል፥ በእጅዋም ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል ቍርባን፥ ለቅንዓት ቍርባን፥ ያኖራል፤ በካህኑም እጅ እርግማንን የሚያመጣው መራራ ውኃ ይሆናል። 19ካህኑም ያምላታል፥ ሴቲቱንም እንዲህ ይላታል፦ ሌላ ወንድ አልተኛሽ፥ ባልሽንም አልተውሽ፥ ራስሽንም አላረከስሽ እንደ ሆነ፥ እርግማንን ከሚያመጣ ከዚህ መራራ ውኃ ንጹሕ ሁኚ፤ 20ነገር ግን ባልሽን ትተሽ ረክሰሽ እንደ ሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ከወንድ ጋር ተኝተሽ እንደሆነ፤ 21ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፥ ካህኑም ሴቲቱን፦ እግዚአብሔር ጭንሽን እያሰለሰለ ሆድሽንም እየነፋ፥ እግዚአብሔር ለመርገምና ለመሐላ በሕዝብሽ መካከል ያድርግሽ፤ 22እርግማንንም የሚያመጣ ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ሆድሽንም ይንፋው፥ ጭንሽንም ያበስብሰው ይላታል፤ ሴቲቱም፦ አሜን አሜን ትላለች። 23ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ይጽፈዋል፥ በመራራውም ውኃ ይደመስሰዋል፤ 24እርግማን የሚያመጣውንም መራራ ውኃ ለሴቲቱ ያጠጣታል፤ የእርግማኑም ውኃ በገባባት ጊዜ መራራ ይሆናል። 25ካህኑም የቅንዓቱን የእህል ቍርባን ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፥ የእህሉንም ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤ 26ካህኑም ከእህሉ ቍርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፥ ከዚያም በኋላ ለሴቲቱ ውኃውን ያጠጣታል። 27ውኃውን ካጠጣት በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ረክሳና በባልዋ ላይ አመንዝራ እንደ ሆነች፥ እርግማንን የሚያመጣው ውኃ ገብቶ መራራ ይሆንባታል፥ ሆድዋም ይነፋል፥ ጭንዋም ይሰለስላል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች። 28ያልረከሰች ያለ ነውርም እንደ ሆነች፥ ንጹሕ ትሆናለች፥ ልጆችንም ታረግዛለች። 29-30ሴት ባልዋን ትታ በረከሰች ጊዜ፥ ወይም በሰው ላይ የቅንዓት መንፈስ በመጣበት ጊዜ፥ ስለ ሚስቱም በቀና ጊዜ፥ የቅንዓት ሕግ ይህ ነው፤ ሴቲቱንም በእግዚአብሔር ፊት ያቁማት፥ ካህኑም እንደዚህ ሕግ ሁሉ ያድርግባት። 31ሰውዮውም ከኃጢአት ንጹሕ ይሆናል፥ ሴቲቱም ኃጢአትዋን ትሸከማለች።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 5: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ