የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 8

8
1ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በከተሞቻቸው ነበሩ። ሕዝቡም ሁሉ በውኃው በር ፊት ወዳለው አደባባይ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ያዘዘውን የሙሴን ሕግ መጽሐፍ ያመጣ ዘንድ ጸሐፊውን ዕዝራን ተናገሩት። 2ካህኑም ዕዝራ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ሕጉን በማኅበሩ በወንዶችና በሴቶች አስተውለውም በሚሰሙት ሁሉ ፊት አመጣው። 3በውኃውም በር ፊት ባለው አደባባይ ላይ ቆሞ፥ ወንዶችና ሴቶች የሚያስተውሉም ሲሰሙ፥ ከማለዳ ጀመሮ እስከ ቀትር ድረስ አነበበው፥ የሕዝቡም ሁሉ ጆሮ የሕጉን መጽሐፍ ለመስማት ያደምጥ ነበር። 4ጸሐፊውም ዕዝራ ስለዚህ ነገር በተሠራ በእንጨት መረባርብ ላይ ቆሞ ነበር፥ በአጠገቡ መቲትያ፥ ሽማዕ፥ ዓናያ፥ ኦርዮ፥ ኬልቅያስ፥ መዕሤያ በቀኙ በኩል፥ ፈዳያ፥ ሚሳኤል፥ መልክያ፥ ሐሱም፥ ሐሽበዳና፥ ዘካርያስ፥ ሜሱላም በግራው በኩል ቆመው ነበር። 5ዕዝራም በሕዝቡ ሁሉ ላይ ከፍ ብሎ ሕዝቡ ሁሉ እያዩ መጽሐፉን ገለጠ በገለጠውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ። 6ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ ሕዝቡም ሁሉ እጃቸውን እየዘረጉ፦ አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውንም አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። 7ደግሞ ኢያሱና ባኒ፥ ሰራብያ፥ ያሜን፥ ዓቁብ፥ ሳባታይ፥ ሆዲያ፥ መዕሤያ፥ ቆሊጣስ፥ ዓዛርያስ፥ ዮዛባት፥ ሐናን፥ ፌልያ፥ ሌዋውያኑም ሕጉን ያስተውሉ ዘንድ ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር፥ ሕዝቡም በየስፍራቸው ቆመው ነበር። 8የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፥ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፥ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር።
9ሐቴርሰታ ነህምያም ጸሐፊውም ካህኑ ዕዝራ ሕዝቡንም የሚያስተምሩ ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ፦ ዛሬ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ነው፥ አታልቅሱ እንባም አታፍስሱ አሉአቸው፥ ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ያለቅሱ ነበርና። 10እርሱም፦ ሂዱ፥ የሰባውንም ብሉ፥ ጣፋጩንም ጠጡ፥ ለእነዚያም ላልተዘጋጀላቸው እድል ፈንታቸውን ስደዱ፥ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፥ የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ አላቸው። 11ሌዋውያንም፦ ቀኑ የተቀደሰ ነውና ዝም በሉ፥ አትዘኑም ብለው ሕዝቡን ሁሉ ጸጥ ያደርጉ ነበር። 12ሕዝቡም ሁሉ የተነገረላቸውን ቃል አስተውለዋልና ሊበሉና ሊጠጡ እድል ፈንታም ሊሰድዱ ደስታም ሊያደርጉ ሄዱ።
13በሁለተኛውም ቀን ከሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤቶች አለቆች ካህናቱም ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል ይተረጉምላቸው ዘንድ ወደ ጸሐፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። 14-15በሰባተኛውም ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ ይቀመጡ ዘንድ በከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌምም፦ ወደ ተራራ ሂዱ፥ የዘይትና የበረሀ ወይራ የባርሰነትም የዘንባባም የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ፥ እንደ ተጻፈውም ዳሶችን ሥሩ ብለው ይናገሩ ያውጁም ዘንድ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ። 16ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፥ እያንዳንዱም በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በአደባባዩም ላይ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባዩ ላይ፥ በውኃውም በር አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠራ። 17ከምርኮም የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳስ ሠሩ፥ በዳሱም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌም ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ አላደረጉም ነበር። እጅግም ታላቅ ደስታ ሆነ። 18ከመጀመሪያውም ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉን ሰባት ቀን ያህል አደረጉ፥ በስምንተኛውም ቀን እንደ ሕጉ የተቀደሰ ጉባኤ ነበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ