የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 6:1-9

መጽሐፈ ነህምያ 6:1-9 አማ54

እንዲህም ሆነ፥ ቅጥሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍራሹም አንዳች እንዳልቀረበት ሰንበላጥና ጦብያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ፥ ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን አላቆምሁም ነበር። ሰንባላጥና ጌሳም፦ መጥተህ በኦኖ ቆላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናኝ ብለው ላኩብኝ፥ ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ያስቡ ነበር። እኔም፦ ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም፥ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ስለ ምን ሥራው ይታጐላል? ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው። እንዲህም ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፥ እኔም እንደ ፊተኛው ቃል መለስሁላቸው። ሰንባላጥም እንደ ፊተኛው ጊዜ ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፥ በእጁም ውስጥ፦ አንተና አይሁድ ዓመፅ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል። ደግሞም፦ ንጉሥ በይሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ ነቢያትን አቁመሃል፥ አሁንም ለንጉሡ ይህን ቃል ያወሩለታል፥ እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር የሚል ክፍት ደብዳቤ ነበረ። እኔም፦ አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር ምንም የለም ብዬ ላክሁበት። እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም፦ እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ፥ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ።