የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 6:1-9

መጽሐፈ ነህምያ 6:1-9 አማ05

ሰንባላጥ፥ ጦቢያ፥ ዐረባዊው ጌሼምና ሌሎችም ጠላቶቻችን የቅጽሩን ግንብ ሠርቼ መፈጸሜንና ያልተሠራ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰሙ፤ ይሁን እንጂ በቅጽር በሮቹ ላይ መዝጊያዎችን አላቆምኩም ነበር። ከዚህም የተነሣ ሰንባላጥና ጌሼም በተለይ ኦኖ ተብሎ በሚጠራው ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንድንገናኛቸው መልእክት ላኩብኝ፤ ይህም እኔን ለመጒዳት በተንኰል የተዶለተ ዘዴ ነበር። እኔም “አስቸኳይ ሥራ ስላለብኝ ተግባሬን አቁሜ እናንተ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ወደ እናንተ ለመምጣት ተብሎ ለምን ሥራው ይቆማል?” አልኳቸው። ያንኑም ዐይነት መልእክት በማከታተል አራት ጊዜ ሲልኩብኝ እኔም ተመሳሳዩን መልስ ሰጠኋቸው። ከዚህም በኋላ ሰንባላጥ ከአገልጋዮቹ አንዱን ለአምስተኛ ጊዜ መልእክት አስይዞ ወደ እኔ ላከ፤ የተላከውም ግልጥ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንተና ወገኖችህ የሆኑት አይሁድ ዐመፅ ለማስነሣት ማቀዳችሁንና የቅጽር ግንቦችንም የምትሠሩት በዚሁ ምክንያት መሆኑን ጐረቤቶቻችን በሆኑ ሕዝቦች ዘንድ እንደሚወራ ጌሼም ነግሮኛል፤ ከዚህም ሌላ አንተ ራስህን ለማንገሥ ማሰብህንና፥ የይሁዳ ንጉሥ መሆንህንም በኢየሩሳሌም አንዲያውጁ፥ ነቢያት መሾምህን ጌሼም ጨምሮ ነግሮኛል፤ ይህንንም ወሬ ንጉሠ ነገሥቱ እንደሚሰማ የተረጋገጠ ነው፤ ስለዚህ አንተና እኔ ተገናኝተን በጒዳዩ ላይ ብንወያይበት ይሻላል።” እኔም “ይህ የምትለው ነገር ሁሉ ምንም እውነትነት የሌለውና አንተ ራስህ የፈለሰፍከው ሐሰት ነው” ብዬ መለስኩለት። በዚህም ዐይነት ሥራውን እንድናቆም ለማድረግ ያስፈራሩን ነበር፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ አበርታኝ!” ስል ጸለይኩ።