ነህምያ 6:1-9

ነህምያ 6:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እን​ዲ​ህም ሆነ፤ ቅጥ​ሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍ​ራ​ሹም አን​ዳች እን​ዳ​ል​ቀ​ረ​በት ሰን​ባ​ላ​ጥና ጦቢያ ዓረ​ባ​ዊ​ውም ጌሳም የቀ​ሩ​ትም ጠላ​ቶ​ቻ​ችን ሰሙ፤ ነገር ግን እስ​ከ​ዚያ ጊዜ ድረስ በበ​ሮቹ ውስጥ ሳን​ቃ​ዎ​ቹን አላ​ቆ​ም​ሁም ነበር። ሰን​ባ​ላ​ጥና ጌሳም፥ “መጥ​ተህ በኦኖ ቈላ ውስጥ ባሉት መን​ደ​ሮች እን​ገ​ናኝ” ብለው ላኩ​ብኝ፤ ነገር ግን ክፉ ያደ​ር​ጉ​ብኝ ዘንድ ይመ​ክሩ ነበር። እኔም እን​ዲህ ስል መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላክ​ሁ​ባ​ቸው፥ “እኔ ታላቅ ሥራ እሠ​ራ​ለሁ፤ እወ​ር​ድም ዘንድ አይ​ቻ​ለ​ኝም። ስለ​ምን ወደ እና​ንተ በመ​ም​ጣ​ቴና በመ​ው​ረዴ ሥራው ይታ​ጐ​ላል? ሥራ​ውን እንደ ፈጸ​ምሁ እመ​ጣ​ለሁ።” እን​ዲ​ህም ቃል አራት ጊዜ ላኩ​ብኝ፤ እኔም እንደ ፊተ​ኛው ቃል መለ​ስ​ሁ​ላ​ቸው። ሰን​ባ​ላ​ጥም እንደ ፊተ​ኛው ብላ​ቴ​ና​ውን አም​ስ​ተኛ ጊዜ ላከ​ብኝ፤ በእ​ጁም ውስጥ እን​ዲህ የሚል ግልጥ ደብ​ዳቤ ነበረ፦ “አን​ተና አይ​ሁድ ዓመፃ እን​ድ​ታ​ስቡ፥ ስለ​ዚ​ህም ቅጥ​ሩን እን​ድ​ት​ሠራ፥ ንጉ​ሣ​ቸ​ውም ትሆን ዘንድ እን​ድ​ት​ወ​ድድ በአ​ሕ​ዛብ ዘንድ ተሰ​ም​ቶ​አል። ደግ​ሞም፦ ንጉሥ በይ​ሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ይና​ገሩ ዘንድ ነቢ​ያ​ትን አቁ​መ​ሃል፤ አሁ​ንም ለን​ጉሡ ይህን ቃል ያወ​ሩ​ለ​ታል፤ እን​ግ​ዲህ መጥ​ተህ በአ​ን​ድ​ነት እን​ማ​ከር።” እኔም፥ “አንተ ከል​ብህ ፈጥ​ረ​ኸ​ዋል እንጂ እንደ ተና​ገ​ር​ኸው ነገር አይ​ደ​ለም” ብዬ ላክ​ሁ​በት። እነ​ር​ሱም ሁሉ ሥራው እን​ዳ​ይ​ፈ​ጸም፥ “እጃ​ቸው ይደ​ክ​ማል” ብለው አስ​ፈ​ራ​ሩን፤ ስለ​ዚ​ህም እጆ​ችን አበ​ረ​ታሁ።

ነህምያ 6:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለበሮቹ መዝጊያ ባልገጥምላቸውም እንኳ፣ ቅጥሩን መሥራቴንና የቀረ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረባዊው ጌሳምና የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ ሰንባላጥና ጌሳም፣ “ናና በኦኖ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንገናኝ” ሲሉ ይህችን መልእክት ላኩብኝ። እነርሱ ግን እኔን ለመጕዳት ዐቅደው ነበር። እኔም፣ “ታላቅ ሥራ እየሠራሁ ስለ ሆነ፣ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ትቼው ወደ እናንተ ወርጄ ሥራው ለምን ይቆማል?” በማለት ይህን መልስ የሚያደርሱ መልእክተኞችን ወደ እነርሱ ላክሁ። አራት ጊዜም ይህንኑ ዐይነት መልእክት ላኩብኝ፤ እኔም በእያንዳንዱ ጊዜ ያንኑ መልስ ሰጠሁ። ከዚያም ሰንባላጥ ለዐምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት በረዳቱ ላከብኝ፤ በእጁም ማኅተም የሌለው ያልታሸገ ደብዳቤ ይዞ ነበር፤ የተጻፈበትም እንዲህ የሚል ነበር፤ “አንተና አይሁዳውያን ለማመፅ እንደምትዶልቱና ቅጥሩንም እንደምትሠሩ በሕዝቦች መካከል ተወርቷል፤ ጌሳምም እውነት መሆኑን አረጋግጧል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተወራው መሠረት አንተ ንጉሣቸው እንደምትሆን፣ ስለ አንተም ‘በአይሁድ ንጉሥ አለ’ ብለው በኢየሩሳሌም የሚያውጁ ነቢያትን እንኳ ሳይቀር እንደ ሾምህ ተወርቷል፤ ይህም ነገር ለንጉሡ መድረሱ አይቀርም፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።” እኔም “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” ብዬ መልስ ላክሁበት። ሁሉም፣ “እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል” ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ። እኔ ግን፣ “አሁንም እጄን አበርታ” ስል ጸለይሁ።

ነህምያ 6:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንዲህም ሆነ፥ ቅጥሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍራሹም አንዳች እንዳልቀረበት ሰንበላጥና ጦብያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ፥ ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን አላቆምሁም ነበር። ሰንባላጥና ጌሳም፦ መጥተህ በኦኖ ቆላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናኝ ብለው ላኩብኝ፥ ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ያስቡ ነበር። እኔም፦ ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም፥ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ስለ ምን ሥራው ይታጐላል? ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው። እንዲህም ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፥ እኔም እንደ ፊተኛው ቃል መለስሁላቸው። ሰንባላጥም እንደ ፊተኛው ጊዜ ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፥ በእጁም ውስጥ፦ አንተና አይሁድ ዓመፅ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል። ደግሞም፦ ንጉሥ በይሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ ነቢያትን አቁመሃል፥ አሁንም ለንጉሡ ይህን ቃል ያወሩለታል፥ እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር የሚል ክፍት ደብዳቤ ነበረ። እኔም፦ አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር ምንም የለም ብዬ ላክሁበት። እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም፦ እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ፥ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ።

ነህምያ 6:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሰንባላጥ፥ ጦቢያ፥ ዐረባዊው ጌሼምና ሌሎችም ጠላቶቻችን የቅጽሩን ግንብ ሠርቼ መፈጸሜንና ያልተሠራ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰሙ፤ ይሁን እንጂ በቅጽር በሮቹ ላይ መዝጊያዎችን አላቆምኩም ነበር። ከዚህም የተነሣ ሰንባላጥና ጌሼም በተለይ ኦኖ ተብሎ በሚጠራው ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንድንገናኛቸው መልእክት ላኩብኝ፤ ይህም እኔን ለመጒዳት በተንኰል የተዶለተ ዘዴ ነበር። እኔም “አስቸኳይ ሥራ ስላለብኝ ተግባሬን አቁሜ እናንተ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ወደ እናንተ ለመምጣት ተብሎ ለምን ሥራው ይቆማል?” አልኳቸው። ያንኑም ዐይነት መልእክት በማከታተል አራት ጊዜ ሲልኩብኝ እኔም ተመሳሳዩን መልስ ሰጠኋቸው። ከዚህም በኋላ ሰንባላጥ ከአገልጋዮቹ አንዱን ለአምስተኛ ጊዜ መልእክት አስይዞ ወደ እኔ ላከ፤ የተላከውም ግልጥ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንተና ወገኖችህ የሆኑት አይሁድ ዐመፅ ለማስነሣት ማቀዳችሁንና የቅጽር ግንቦችንም የምትሠሩት በዚሁ ምክንያት መሆኑን ጐረቤቶቻችን በሆኑ ሕዝቦች ዘንድ እንደሚወራ ጌሼም ነግሮኛል፤ ከዚህም ሌላ አንተ ራስህን ለማንገሥ ማሰብህንና፥ የይሁዳ ንጉሥ መሆንህንም በኢየሩሳሌም አንዲያውጁ፥ ነቢያት መሾምህን ጌሼም ጨምሮ ነግሮኛል፤ ይህንንም ወሬ ንጉሠ ነገሥቱ እንደሚሰማ የተረጋገጠ ነው፤ ስለዚህ አንተና እኔ ተገናኝተን በጒዳዩ ላይ ብንወያይበት ይሻላል።” እኔም “ይህ የምትለው ነገር ሁሉ ምንም እውነትነት የሌለውና አንተ ራስህ የፈለሰፍከው ሐሰት ነው” ብዬ መለስኩለት። በዚህም ዐይነት ሥራውን እንድናቆም ለማድረግ ያስፈራሩን ነበር፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ አበርታኝ!” ስል ጸለይኩ።

ነህምያ 6:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንዲህም ሆነ ምንም እንኳ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን ባልገጥምም ቅጥሩን እንደሠራሁ፥ አንድም የፈረሰ እንዳልቀረ ሰንባላጥ፥ ጦቢያና ዓረባዊው ጌሼም የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፥ ሰንባላጥና ጌሼም እንዲህ ብለው ላኩብኝ፦ “ናና በኦኖ ሜዳ ባሉት መንደሮች እንገናኝ፤” ነገር ግን ክፉ ሊያደርሱብኝ አቅደው ነበር። እኔም እንዲህ ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው፦ “ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ መውረድም አልችልም፤ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ሥራው ለምን ይቆማል?” ይህንኑ ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም ይህንኑ ቃል መለስኩላቸው። ከዚህም በኋላ ሰንባላጥ የተከፈተ ደብዳቤ በእጁ አስይዞ ይህንኑ ቃል በአገልጋዩ ለአምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፤ በውስጡ የተጻፈውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንተና አይሁድ ልታምጹ እንዳቀዳችሁ፥ ለዚህም ቅጥሩን እንደሠራህ፥ ንጉሣቸውም ልትሆን እንደምትፈልግ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል ጌሼምም ብሎታል። ‘ንጉሥ በይሁዳ አለ’ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም እንዲናገሩ ነቢያትን ሾመሃል፤ አሁንም ይህን ነገር በንጉሡ ዘንድ ይሰማል፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።” እኔም እንዲህ ብዬ ላክሁበት፦ “አንተ ከምትለው ነገር አንድም አልተደረገም፥ አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋልና” ሁሉም እንዲህ እያሉ አስፈራሩን፦ “ከሥራው እጃቸውን ያላላሉ፥ አይሠራምም” አሁንም እጄን አበርታ።