መጽሐፈ ነህምያ 5
5
1በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ። 2አያሌዎቹም፦ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ብዙዎች ናቸው፥ በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት ይሉ ነበር። 3አያሌዎቹም፦ ከራብ የተነሣ እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንና ወይናችንን ቤታችንንም አስይዘናል ይሉ ነበር። 4ሌሎቹም፦ ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፥ 5አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፥ እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፥ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ፥ ታላላቆችም እርሻችንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም ይሉ ነበር።
6እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቈጣሁ። 7በልቤም አሰብሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም፦ ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ ብዬ ተጣላኋቸው፥ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። 8እኔም፦ ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፥ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን? አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፥ መልስም አላገኙም። 9ደግሞም አልሁ፦ የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፥ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን? 10እኔም ደግሞ ወንድሞቼም ብላቴኖቼም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል፥ እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው። 11እርሻቸውንና ወይናቸውን ወይራቸውንና ቤታቸውንም ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን ከመቶ እጅ አንድ እጅ እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው። 12እነርሱም፦ እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንሻም፥ እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። 13ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፦ ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፥ እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፦ አሜን አሉ፥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፥ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ።
14ንጉሡም በይሁዳ ምድር ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ካዘዘኝ ጊዜ ጀምሮ ከንጉሡ ከአርጤክስስ ከሀያኛው ዓመት እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ አሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞቼ ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልበላንም። 15ከእኔ አስቀድመው የነበሩት አለቆች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደው ነበር፥ ስለ እንጀራውና ስለ ወይኑ አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፥ ሎሌዎቻቸውም ደግሞ በሕዝቡ ላይ ይሠለጥኑ ነበር፥ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም። 16ደግሞም አጥብቄ የቅጥሩን ሥራ ሠራሁ፥ እርሻም አልገዛንም፥ ብላቴኖቼም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ። 17ደግሞም በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ ወደ እኛ ከመጡት ሌላ ከአይሁድና ከሹማምቱ መቶ አምሳ ሰዎች በገበታዬ ነበሩ። 18ከወፎችም በቀር ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች፥ በአሥር በአሥር ቀንም ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር፥ ነገር ግን አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ከብዶ ነበርና ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልሻም ነበር። 19አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያድረግሁትን ሁሉ ለበጎነት አስብልኝ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነህምያ 5: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ