የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 4:1-14

መጽሐፈ ነህምያ 4:1-14 አማ54

ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድም አላገጠ። በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት፦ እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድር ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? ብሎ ተናገረ። አሞንዊውም ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ፦ በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል አለ። አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፥ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፥ በምርኮ አገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው። በደላቸውንም አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፥ በሠራተኞች ፊት አስቆጥተውሃልና። ቅጥሩንም ሠራን፥ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኩሌታው ድረስ ተጋጠመ፥ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ። ሰንበላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ። ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን። ይሁዳም፦ የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፥ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ። ጠላቶቻችንም፦ ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ ሥራቸውንም እስክናስተጓጉል ድረስ አያውቁምና አያዩም አሉ። በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው፦ ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው አሥር ጊዜ ነገሩን። ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው። አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ፦ አትፍሩአቸው፥ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው።