ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፥ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። ቃሉንም ይዘው፦ ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። እነርሱም፦ ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። እርሱም መልሶ፦ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናናል፤ ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ደግሞ መጥቶአል፥ ስለ እርሱም እንደ ተጸፈ የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት አላቸው። ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ሲከብቡአቸው ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አየ። ወዲያውም ሕዝቡ ሁሉ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፥ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። ጻፎችንም፦ ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ከሕዝቡ አንዱ መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፥ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፥ አልቻሉምም አለው። እርሱም መልሶ፦ የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው። ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። አባቱንም፦ ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው። ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ። ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና፦ አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፥ ከእርሱ ውጣ እንግዲህም አትግባበት አለው። ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም፦ ሞተ እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው ቆመም። ወደ ቤትም ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ፦ እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው? ብለው ብቻውን ጠየቁት። ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም አላቸው።
የማርቆስ ወንጌል 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 9:2-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos