የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 9:2-29

ማርቆስ 9:2-29 NASV

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረዥም ተራራ ይዟቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ፤ በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም በምድር ላይ ማንም ዐጣቢ ዐጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወድደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም። ከተራራው ላይ በሚወርዱበትም ጊዜ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፣ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ከዚያም፣ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉን ነገር እንደ ነበረ ያደርጋል፤ ታዲያ፣ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ያሻቸውን ሁሉ አድርገውበታል።” ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከብበዋቸው፣ ጸሐፍት ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አዩ። ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ። እርሱም፣ “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት ስለ ምን ጕዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ ዐድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ ዐረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፣ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፣ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፣ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣቱን ባየ ጊዜ፣ “አንተ ደንቈሮና ድዳ መንፈስ ከእርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዝሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎቹ “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው፣ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የዚህ ዐይነቱ ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም ብቻ ነው” አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች