እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ። ብቻውንም በሆነ ጊዜ፥ በዙሪያው የነበሩት ከአሥራ ሁለቱ ጋር ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እንዲህም አላቸው፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን፥ አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፥ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፥ እንዳይመለሱ ኃጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል። አላቸውም፦ ይህን ምሳሌ አታውቁምን? እንዴትስ ምሳሌዎቹን ሁሉ ታውቃላችሁ? ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው፥ በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል። እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።
የማርቆስ ወንጌል 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 4:3-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos