የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 4:3-20

ማርቆስ 4:3-20 NASV

“ስሙ፤ አንድ ዘሪ ዘር ሊዘራ ወጣ። ዘሩን በሚዘራበትም ጊዜ አንዳንዱ መንገድ ላይ ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። ሌላው በቂ ዐፈር በሌለበት በጭንጫ ቦታ ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አድጎ የዘሩን ተክል ስላነቀው ፍሬ አላፈራም። ሌላው ዘር ደግሞ በመልካም መሬት ላይ ስለ ወደቀ በቅሎ አደገ፤ ፍሬም ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፣ አንዱ ስድሳ፣ ሌላውም መቶ ፍሬ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ፣ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። ብቻውን በሆነ ጊዜ፣ ዐሥራ ሁለቱና አብረውት የነበሩት ሌሎች ስለ ምሳሌዎቹ ጠየቁት። እርሱም፣ “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ነገር ሁሉ በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ ይኸውም፣ “ ‘ማየቱን እንዲያዩ እንዳያስተውሉትም፣ መስማቱን እንዲሰሙ ልብ እንዳይሉትም፣ እንዳይመለሱና ኀጢአታቸው እንዳይሰረይላቸው ነው’ አላቸው።” ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ምሳሌ አልተረዳችሁትምን? ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ዘሪው ቃሉን ይዘራል። አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ላይ የወደቀውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል። እንዲሁም ሌሎች በጭንጫ ቦታ ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ ነገር ግን ሥር የሌላቸው ስለ ሆኑ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። ሌሎቹ ደግሞ በእሾኽ መካከል የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን መስማት ይሰማሉ፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን ዐንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል። ሌሎቹ በመልካም መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ እነዚህም ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች