የማርቆስ ወንጌል 2:18-28

የማርቆስ ወንጌል 2:18-28 አማ54

የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም፦ የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም አላቸው፦ ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም። ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ። በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ። በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። ፈሪሳውያንም፦ እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት። እርሱም፦ ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። ደግሞ፦ ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች