የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 2:18-28

ማርቆስ 2:18-28 NASV

የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር፤ አንዳንድ ሰዎችም መጥተው ኢየሱስን፣ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ሲጾሙ፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋራ እያለ ዕድምተኞቹ ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋራ እያለ ሊጾሙ አይችሉም፤ ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያም ጊዜ ይጾማሉ። “በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ቍራጭ ጨርቅ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፣ አዲሱ ጨርቅ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሰፋል። እንዲሁም አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ የሚያስቀምጥ የለም፤ ይህ ከተደረገማ የወይን ጠጁ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም አቍማዳውም ይበላሻሉ። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ መቀመጥ ያለበት በአዲስ አቍማዳ ነው።” በሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ሲያልፍ፣ ዐብረውት በመጓዝ ላይ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። ፈሪሳውያንም፣ “እነሆ፤ በሰንበት ቀን ለምን ያልተፈቀደውን ነገር ያደርጋሉ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊት በተራበና የምግብ ፍላጎት በጸናበት ጊዜ ዐብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋራ ያደረገውን አላነበባችሁምን? በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፣ ካህናት ብቻ እንዲበሉት የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ለርሱም ሆነ ዐብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ፣ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም፤ ስለዚህ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች