የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 15:15-41

የማርቆስ ወንጌል 15:15-41 አማ54

ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሕፈትም፦ የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር። ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። መጽሐፍም፦ ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ። የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና፦ ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ፦ ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር። ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው። በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው፦ እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ። አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ፦ ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ። የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ፦ ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። ሴቶችም ደግሞ በሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ መግደላዊት ማርያም የታናሹ ያዕቆብና የዮሳም እናት ማርያም ሰሎሜም ነበሩ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የወጡ ሌሎች ብዙዎች ሴቶች ነበሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች