የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 15:15-41

የማርቆስ ወንጌል 15:15-41 አማ05

ጲላጦስ ሰዎቹን ደስ ለማሰኘት ብሎ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን አስገረፈውና እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ የቀሩትንም ወታደሮች ሁሉ ጠሩ፤ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊልም ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበትና፤ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ በማፌዝ እጅ ይነሡት ነበር። በመቃ ራስ ራሱን ይመቱት ነበር፤ ምራቃቸውንም እንትፍ ይሉበት ነበር፤ በፊቱም በማላገጥ እየተንበረከኩ ይሰግዱለት ነበር። ካፌዙበትም በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው፥ የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲሄዱም ሳሉ የቀሬና ሰው የሆነውን የእስክንድርንና የሩፎስን አባት ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚያም በኋላ ኢየሱስን ትርጒሙ የራስ ቅል ወደ ሆነው ስፍራ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። እዚያም ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣም። ከዚህም በኋላ ሰቀሉት፤ ልብሶቹንም ማን ምን እንደሚወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉት። ኢየሱስን ሲሰቅሉት ጊዜው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። ወንጀሉንም ለማመልከት “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ነበር። ከኢየሱስም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አምጥተው አንዱን በቀኙ፥ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። [ በዚህም ሁኔታ “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤” የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጸመ።] በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች ራሳቸውን በንቀት እየነቀነቁ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር፦ “አዬ፥ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው! እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!” በዚህ ዐይነት የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራንም እርስ በርሳቸው እንዲህ እየተባባሉ ይዘባበቱበት ነበር፦ “ሌሎችን አድኖአል፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! እርሱ መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንይና እንመንበት!” እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር። ከቀኑም ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ትርጓሜውም “አምላኬ፥ አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ የእርሱን ጩኸት ሰምተው “እነሆ! ኤልያስን ይጠራል፤” አሉ። ከእነርሱም አንዱ ሮጠና ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ፤ እንዲጠጣውም በመቃ ላይ አድርጎ ለኢየሱስ ሰጠውና “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደ ሆነ እንይ!” አለ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ነፍሱም ከሥጋው ተለየች። የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። በመስቀሉ ፊት ለፊት ቆሞ የነበረ የመቶ አለቃ ኢየሱስ እንዴት ነፍሱ ከሥጋው እንደ ተለየች ባየ ጊዜ፥ “ይህ ሰው በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፤” አለ። በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ፥ አንዳንድ ሴቶችም በዚያ ነበሩ። ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፥ ሰሎሜም ይገኙ ነበር። እነርሱ ኢየሱስ በገሊላ በነበረበት ጊዜ፥ ይከተሉትና ያገለግሉት ነበር። እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ብዙ ሌሎች ሴቶች ነበሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች