የማርቆስ ወንጌል 11:20-33

የማርቆስ ወንጌል 11:20-33 አማ54

ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት። ጴጥሮስም ትዝ ብሎት፦ መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በእግዚአብሔር እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። ደግሞም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እርሱም በመቅደስ ሲመላለስ፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ እነዚህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። ኢየሱስም፦ እኔም አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም መልሱልኝ፥ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ አላቸው። እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ፦ ከሰማይ ነው ብንል፦ እንግዲያውስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ነገር ግን፦ ከሰው ነው እንበልን? አሉ፤ ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና ሕዝቡን ፈሩ። ለኢየሱስም መልሰው፦ አናውቅም አሉት ኢየሱስም፦ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች