የማርቆስ ወንጌል 11:20-33

የማርቆስ ወንጌል 11:20-33 አማ05

በማግስቱ ማለዳ በመንገድ ሲያልፉ የበለሲቱ ዛፍ ከነስርዋ ደርቃ አዩአት። ጴጥሮስም ነገሩ ትዝ ብሎት ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! እነሆ፥ የረገምሃት ዛፍ ደርቃለች” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ሰው በልቡ ሳይጠራጠር የሚፈልገው ነገር እንደሚፈጸምለት አምኖ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር፤’ ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ በጸሎት ማናቸውንም ነገር ብትለምኑ፥ እንደ ተፈጸመላችሁ አድርጋችሁ እመኑ፤ የምትለምኑትም ሁሉ ይሰጣችኋል። በሰማይ ያለው አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ እናንተም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ ሰው በአንዳች ነገር አስቀይሞአችሁ ከሆነ ይቅርታ አድርጉለት። እናንተ የሌሎችን በደል ይቅር ባትሉ ግን በሰማይ ያለው አባታችሁ የእናንተንም ኃጢአት ይቅር አይልላችሁም።” እንደገናም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ የካህናት አለቆች፥ የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጡና “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይስ እነዚህን ነገሮች እንድታደርግ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተ መልስ ከሰጣችሁኝ፥ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ነበረ ወይስ ከሰው? እስቲ መልሱልኝ፤” አላቸው። እነርሱም “እንግዲህ ምን እንበል?” በማለት እርስ በርሳቸው ተመካከሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው፥’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው ነው፥’ ብንልሳ?” ይህን እንዳይሉ ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን በእርግጥ ነቢይ ነው ይሉ ስለ ነበር ፈሩ። ስለዚህ “እኛ አናውቅም።” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም፤” አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች