የማርቆስ ወንጌል 1:35-45

የማርቆስ ወንጌል 1:35-45 አማ54

ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ። ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩትም ገሥግሠው ተከተሉት፥ ባገኙትም ጊዜ፦ ሁሉ ይፈልጉሃል አሉት። እርሱም፦ በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና አላቸው። በምኵራባቸውም እየሰበከ አጋንንትንም እያወጣ ወደ ገሊላ ሁሉ መጣ። ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ ተንበረከከና፦ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው። ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፦ እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው። በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀውና ነጻ። በብርቱም ተናግሮ ወዲያው አወጣው፤ ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ አለው። እርሱ ግን ሲወጣ ብዙ ሊሰብክና ነገሩን ሊያወራ ጀመረ፥ ስለዚህም ኢየሱስ ተገልጦ ወደ ከተማ መግባት ወደ ፊት ተሳነው፥ ነገር ግን በውጭ በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ከየስፍራውም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች