የማርቆስ ወንጌል 1:35-45

የማርቆስ ወንጌል 1:35-45 አማ05

ሊነጋ ሲል፥ ኢየሱስ በማለዳ ተነሥቶ ወጣና ለመጸለይ ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ሄደ፤ ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እርሱን ፍለጋ ወጥተው ሄዱ። ባገኙትም ጊዜ፥ “ሰዎች ሁሉ ይፈልጉሃል” አሉት። ኢየሱስም፦ “እኔ የመጣሁት ለማስተማር ስለ ሆነ ወንጌልን እንዳስተምር በቅርብ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ!” አላቸው። ስለዚህ በየምኲራቦቻቸው እያስተማረና አጋንንትን እያስወጣ በገሊላ ሁሉ ይዘዋወር ነበር። አንድ ለምጻም ወደ ኢየሱስ መጣና በእግሩ ሥር ተንበርክኮ፦ “ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፤” ሲል ለመነው። ኢየሱስም ራራለትና እጁን ዘርግቶ እየዳሰሰው፥ “ፈቅጃለሁ፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ኢየሱስ ሰውዬውን በጥብቅ አስጠንቅቆ አሰናበተው፤ “ይህን ነገር ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለሕዝቡም ምስክር እንዲሆን ስለ መዳንህ ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ፤” ብሎ አዘዘው። ይሁን እንጂ ሰውየው ከዚያ ወጥቶ ይህን ነገር ለሰው ሁሉ ማውራት ጀመረ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ወደ ማናቸውም ከተማ በግልጥ መግባት አልቻለም። ነገር ግን ከከተማ ውጪ ሰው በሌለበት ቦታ ይኖር ነበር፤ ሆኖም ሰዎች ከየስፍራው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች