የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 27:11-23

የማቴዎስ ወንጌል 27:11-23 አማ54

ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም፦ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም፦ አንተ አልህ አለው። የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ፦ ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው። ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም። በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ፦ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። ገዢውም መልሶ፦ ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም፦ በርባንን አሉ። ጲላጦስ፦ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም፦ ይሰቀል አሉ። ገዢውም፦ ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን፦ ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች