ማቴዎስ 27:11-23
ማቴዎስ 27:11-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ አልህ፤” አለው። የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ “ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን?” አለው። ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም። በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ “በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?” አላቸው፤ በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ “ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ፤” ብላ ላከችበት። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። ገዢውም መልሶ “ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም “በርባንን” አሉ። ጲላጦስ “ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው?” አላቸው፤ ሁሉም “ይሰቀል!” አሉ። ገዢውም “ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው?” አለ፤ እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ ጩኸት አበዙ።
ማቴዎስ 27:11-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አገረ ገዥው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዥውም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አንተው እንዳልኸው ነው” ሲል መለሰለት። የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲከስሱት ግን ምንም መልስ አልሰጠም። በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከስሱህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም። አገረ ገዥው ሕዝቡ በበዓሉ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜ በዐመፅ የታወቀ በርባን የሚባል እስረኛ ነበር። ሕዝቡ እንደ ተሰበሰቡ ጲላጦስ፣ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ከኢየሱስ፣ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ ጲላጦስም በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፣ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለ ተሠቃየሁ፣ በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በርባን እንዲፈታላቸው ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይለምኑ ዘንድ ሕዝቡን ያግባቡ ነበር። አገረ ገዥውም፣ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀ። እነርሱም፤ “በርባንን!” በማለት መለሱ። ጲላጦስም፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም፣ “ይሰቀል!” አሉ። ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን ክፉ ነገር አድርጓል?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱ ግን አብዝተው እየጮኹ፣ “ይሰቀል!” አሉ።
ማቴዎስ 27:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም፦ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም፦ አንተ አልህ አለው። የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ፦ ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው። ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም። በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ፦ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። ገዢውም መልሶ፦ ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም፦ በርባንን አሉ። ጲላጦስ፦ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም፦ ይሰቀል አሉ። ገዢውም፦ ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን፦ ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ።
ማቴዎስ 27:11-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ወደ ገዢው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀረበ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው” ሲል መለሰ። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲወነጅሉት ምንም መልስ አልሰጠም። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ “በስንት ነገር ሲወነጅሉህ አትሰማምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ገዢው እስኪደነቅ ድረስ ለአንዲት ክስ እንኳ ቃል አልመለሰለትም። ገዢው በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሕዝቡ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ፈቶ መልቀቅ አስለምዶ ነበር። በዚያን ጊዜ “በርባን” የተባለ በዓመፀኛነቱ የታወቀ እስረኛ ነበረ። ስለዚህ ሰዎቹ በተሰበሰቡ ጊዜ ጲላጦስ፥ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን ነውን ወይስ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን?” ሲል ጠየቃቸው። ይህን ያለበት ምክንያት ኢየሱስን በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ስለ ነበር ነው። ከዚህም በላይ ጲላጦስ በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ ሌሊት በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ በንጹሕ ሰው ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች “በርባን ይለቀቅ! ኢየሱስ ይገደል!” ብለው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አግባቡ። ገዢውም “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ሕዝቡን እንደገና ጠየቀ። እነርሱም “በርባንን እንድትፈታልን እንፈልጋለን” ሲሉ መለሱ። ጲላጦስም “ታዲያ፥ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም “ይሰቀል!” ሲሉ መለሱ። ገዢውም ለምን? “እርሱ ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ አብዝተው ጮኹ።
ማቴዎስ 27:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስ በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ አልህ” አለው። በሊቃነ ካህናትና በሽማግሌዎች ሲከሰስ ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ “ስንት ነገር እንደሚመሰክሩብህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰለትም፤ በዚህም ገዢው እጅግ ተደነቀ። በዚያ በዓል፥ ገዢው ሕዝቡ የወደደውን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜ በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። ስለዚህ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ “ማንን ልፍታላችሁ ኢየሱስ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን?” አላቸው። በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ፥ ሚስቱ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ ጻድቅ ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት። ሊቃነ ካህናቱና ሽማግሌዎቹ ግን በርባን እንዲለቀቅ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፋ ሕዝቡን አግባቡ። ገዢውም መልሶ “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም “በርባንን” አሉ። ጲላጦስም “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው፤ ሁሉም “ይሰቀል!” አሉ። እርሱም “ምን ክፉ ነገር ሠራና?” አለ፤ እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ አብዝተው ጮኹ።