የማቴዎስ ወንጌል 22:23-46

የማቴዎስ ወንጌል 22:23-46 አማ54

በዚያን ቀን፦ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥ እንዲህም ብለው ጠየቁት፦ መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ። ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤ እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች። ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች? ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ። በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም። ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን፦ እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። ሕዝቡም ይህን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ። ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው፦ መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል። ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ፦ ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። እርሱም፦ እንኪያስ ዳዊት፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው። አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች