በዚያው ቀን፣ ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ ብለው ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ ሙሴ፣ ‘አንድ ሰው ከሚስቱ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት አግብቶ ለርሱ ዘር ይተካለት’ ብሏል። በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ፣ ሚስቱን ወንድሙ አገባት፤ እንደዚሁ ደግሞ ሁለተኛውም፣ ሦስተኛውም እስከ ሰባተኛው ድረስ በዚህ ሁኔታ ሞቱ። በመጨረሻ ሴትዮዋ ራሷ ሞተች። ስለዚህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ቀን ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ ትስታላችሁ፤ ከትንሣኤ በኋላ ሰዎች እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም። ስለ ሙታን ትንሣኤ ግን እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ የተናገራችሁን አላነበባችሁምን? ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ።’ እግዚአብሔር የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ በትምህርቱ ተደነቁ። ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ሰምተው፣ ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ከእነርሱም አንድ የኦሪት ሕግ ዐዋቂ፣ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትእዛዝ ነው?” እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዞች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ፣ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው?” እነርሱም፣ “የዳዊት ልጅ ነው” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ታዲያ፣ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ለምን ‘ጌታዬ’ ይለዋል? ለምንስ፣ እንዲህ ይለዋል? “ ‘ጌታ ጌታዬን፤ “ጠላቶችህን ከእግሮችህ በታች እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ።” ’ ስለዚህ ዳዊት፣ ‘ጌታዬ’ ብሎ ከጠራው፣ እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” አንድ ቃል ሊመልስለት የቻለ ወይም ከዚያ ቀን ጀምሮ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።
ማቴዎስ 22 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 22
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 22:23-46
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች