የማቴዎስ ወንጌል 22:23-46

የማቴዎስ ወንጌል 22:23-46 አማ05

በዚያኑ ቀን፥ “የሙታን ትንሣኤ የለም” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ! ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አግብቶ ለሟቹ ዘር ይተካለት፤’ ብሎአል። ሰባት ወንድማማቾች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ የሁሉም ታላቅ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ስለዚህ ታናሽ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አገባ። እንዲሁ ሁለተኛውም፥ ሦስተኛውም እስከ ሰባተኛው ድረስ በየተራ አግብተዋት ሞቱ። ከሁሉም በኋላ ሴትዮዋ ሞተች። ታዲያ፥ ሰባቱም ስለ አገቡአት ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቃችሁ ትሳሳታላችሁ። በሙታን ትንሣኤ ጊዜ ሰዎች በሰማይ እንዳሉት መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም። ደግሞ ስለ ሙታን መነሣት እግዚአብሔር ለእናንተ የነገራችሁን አላነበባችሁምን? እርሱም ያለው እንዲህ ነው፦ ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ ስለዚህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ በትምህርቱ ተደነቁ። ኢየሱስ ሰዱቃውያንን መልስ አሳጥቶ ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ የሕግ መምህር፥ ኢየሱስን ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “መምህር ሆይ! ከሕግ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ አምላክህን በሙሉ ልብህ፥ በሙሉ ነፍስህ፥ በሙሉ ሐሳብህ ውደድ፤ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው። ይህንንም የሚመስለው ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ የሚለው ነው። የሕግና የነቢያት ትምህርት ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዞች ላይ ነው።” ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “ስለ መሲሕ ምን ትላላችሁ? የማንስ ልጅ ይመስላችኋል?” እነርሱም “የዳዊት ልጅ ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ታዲያ፥ ዳዊት በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ በተናገረ ጊዜ እንዴት ‘ጌታ’ ብሎ ጠራው? ‘እግዚአብሔር ለጌታዬ ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ!’ አለው። እንግዲህ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው ታዲያ መሲሕ እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” በዚህ አንድ ቃል እንኳ ሊመልስለት የቻለ ማንም ሰው አልነበረም፤ ከዚያን ቀን ጀምሮም ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም አልነበረም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች