የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50

የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50 አማ54

ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው። ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና፦ እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን? አሉ። ፈሪሳውያን ግን ሰምተው፦ ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ። ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኵኦነናለህ። በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና፦ መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም። በዚያን ጊዜም፦ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል። ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንዱም፦ እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል አለው። እርሱ ግን ለነገረው መልሶ፦ እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው። እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፦ እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች

Free Reading Plans and Devotionals related to የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50